በሰሜን ሸዋ ዞን ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጀ
ደብረ ብርሃን፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአርሶ አደሩ ተሳትፎ ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የአፈር ለምነት ማሻሻያና ማስፋፊያ ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ዘለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን በማሳደግና እርጥበትን በመያዝ ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከ10 ሚሊዮን 145 ሺህ ሜትሪክ ኩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ገልጸው፣ አስካሁንም ከ9 ሚሊዮን 983 ሺህ ሜትሪክ ኩብ በላይ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።
በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅቱ 356ሺህ 412 አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም ወይዘሮ እመቤት ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከባዮ ጋዝ ተረፈ ምርት ቨርሚ ኮምፖስት በማዘጋጀት የአርሶ አደሩን የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ 278 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት አርሶ አደሩ ለዘመናዊ ማዳበሪያ የሚያወጣን ወጪ ከማስቀረት ባለፈ ገንዘቡን ለሌሎች ገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲያውለው ያስችላል ብለዋል።
በዞኑ የባሶና ወራና ወረዳ ዘንደጉር ቀበሌ አርሶ አደር አለመ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በአካባቢያቸው የሚገኘውን የእጽዋትና የእንስሳት ተረፈ ምርት ተጠቅመው ያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርታማነታቸውን እያሳደገላቸው ነው።
ባለፈው በጀት ዓመት 20 ሜትሪክ ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው መጠቀማቸውን ገልጸው፣ በዚህም ለዘመናዊ ማዳበሪያ ግዥ ሲያወጡት የነበረውን ወጭ እንዳዳኑ ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት ልምድ በመነሳት ዘንድሮ 40 ሜትሪክ ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርታማነታቸውን ለማሳደግና ወጪያቸውን ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚሁ ወረዳ የጭብሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቄስ ጌታነሀ ይርጉ እንዳሉት ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ሙያዊ እገዛ መሰረት ሁለት ሜትሪክ ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከመምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ ኮምፖስት ተዘጋጅቶ ለመስኖና ለመኸር ሰብል ልማት ውሏል።