ወጣቶች የፈጠራ ስራዎችን በማበልፀግ በዘርፉ ውጤታማ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የፈጠራ ስራዎችን በማበልፀግ በዘርፉ ውጤታማ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ህዳር 1/2018 (ኢዜአ)፦ወጣቶች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ስራዎችን በማበልፀግ በዘርፉ ውጤታማ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለፁ።
ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚካሔደው 10ኛው አገር አቀፍ የወጣቶች የፈጠራ ስራ ውድድር የማስጀመሪያ መረሃ-ግብር ተካሒዷል።
የውድድር መረሃ ግብሩን አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንደገለጹት፤ መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያ በሚል መርህ ለሳይንስ፣ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በተለይም የቴክኖሎጂ ዘርፉ በአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጉላት በርካታ ተግባራት መከናወኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የዘርፉን የአሰራር ስርዓት ማሻሻል የሚያስችሉ የፖሊሲና የሪፎርም ስራዎች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር የሚዘጋጀው የፈጠራ ስራ ውድድር አንዱ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ አብራርተዋል።
በዚህ ውድድር የሚወጡ የፈጠራ ስራዎች ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸው እውቀትና አቅም ከፍ እያለ መምጣቱን በተግባር የሚያሳይ ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለው ገልፀዋል።
ወጣቶች የማህበረሰቡን ችግር የሚያቃልሉ የፈጠራ ስራዎችን በማበልፀግ በዘርፉ የሚኖረውን ተወዳዳሪነት ከፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።