ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይከናወናሉ-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤ህዳር 1/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በሁሉም ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በተከናወኑ የልማት፣የሰላም ግንባታና ሌሎች ስራዎችና በቀጣይ ወራት የተያዙትን እቅዶች የገመገመ መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩም በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ የልማት፣የሰላም ግንባታ፣ህግ የማስከበር፣ የኮሪደር ልማት፣የመንገድ ግንባታና ሌሎች የህዝቡን ተጠቃሚነትና የክልሉን የብልጽግና ጉዞ የሚያጎለብቱ ስራዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፥ በክልሉ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በተለይም በክልሉ ባለፉት ጊዜያት ለማከናወን የታቀዱ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ቢያሳዩም በአንዳንድ ስራዎች ላይ ግን ክፍተት መታየቱን አንስተዋል።

ለዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስና ቅንጅታዊ አሰራርን አለማዳበር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመው፥ ይህንንም በቀጣይ በመፈጸም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግና የብልጽግናን ጎዞ ማሳለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይም በቀጣይ አመራሩ የኑሮ ውድነትን የመቀነስ፤ ሌብነት፣ መንደርተኝነት፣ ጽንፈኝነትንና ጠባቂነትን የመታገልና የመቀነስ እንዲሁም ተረጂነትን፣ ኮንትሮባንድና የጸረ ሰላም ሃይሎችን እኩይ ተግባራትን ዜሮ ማድረስ ይገባል ብለዋል።


 

የበጋ ወራት የልማት ስራዎችና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ደግሞ ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አንስተው፤ የኮደርስ ስልጠናና የፋይዳ መታወቂያን ለዜጎች የማዳረስ ስራዎችንም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የምርት ማከማቻ፣ የቱሪስት መዳረሻ፣ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ እና የሽያጭ ማዕከላት ግንባታም ጊዜ ሳይሰጣቸው መከናወን የሚገባቸው መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም አዳዲስ የሚከናወኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋት፣ በከተማና በገጠር የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ እና አዳዲስ የሚገነቡትንም በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል።

አመራሩ የተቀመጡትን የልማት አቅጣጫዎች ፍጥነት በማስቀጠልና ፈጠራን በማከል በተገቢው ጊዜና በጥራት ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ እንዲሁም የወረዳ አመራር አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም