ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከባህል ማስተዋወቅ ባሻገር ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሀገሪቱ የሚገኙ የብዝኃ ባህልና ቋንቋን ከማስተዋወቅ ባለፈ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት መድረክ መሆኑን የኢፌዴሪ የህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ፡፡ 

የዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል ፡፡ 

ኢትዮጵያ የብዝኃ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና እምነቶች መገኛ ሀገር ናት። 

ብዝኃ ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክና እምነት ያላቸው ብሔረሰቦች ተዋድደውና ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩባት የሕብረ-ብሔራዊነት ተምሳሌትም ናት።

የኢፌዴሪ የህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነታቸው የቃል ኪዳን ሰነድ ህገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን መሆኑን ተናግረዋል።

ዕለቱም በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ የሚተዋወቁበትና ልምድ የሚለዋወጡበት ምቹ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡ 

ይህም እንደ ሀገር ያለው ብዝኃ ባህልና ቋንቋ ሀብት ከማስተዋወቅም ባለፈ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበት መድረክ ነው ብለዋል።  


 

በህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና አሰልጣኝ አቶ ተስፋዬ መገርሳ በበኩላቸው፣ ህዳር 29 በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን አብሮነትና አንድነት እያፀኑና እያጠናከሩ የሚሄዱበት ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን የጠበቀች በቀጠናውም ሆነ በዓለም ደረጃ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል። 

ከለውጡ ወዲህ የበዓሉ አከባበር ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አብሮነት፣ አንድነትና ህብረ-ብሔራዊነትን የሚያጠናክሩ የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታና በሌሎችም ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የሕዝብ ትብብርና ቅንጅት ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ የመሆናቸው ማሳያና መገለጫ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በተመረቀበት ማግስት መሆኑ ልዩና ታሪካዊ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም