በሰው ተመርተን መጥተን በራሳችን ተመልሰናል-ታካሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሰው ተመርተን መጥተን በራሳችን ተመልሰናል-ታካሚዎች
ደሴ ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ በደሴ ከተማ ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል በተደረገላቸው ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና በሰው ተመርተው መጥተው የዓይን ብርሃናቸው ተመልሶ በራሳቸው መመለስ በመቻላቸው መደሰታቸውን ታካሚዎች ገለጹ።
ሆስፒታሉ ለአንድ ሳምንት በዘመቻ በሰጠው ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና አንድ ሺህ 730 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል።
ታካሚዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፤ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና በሰው ተመርተው መጥተው የዓይን ብርሃናቸው ተመልሶ በራሳቸው መመለስ በመቻላቸው ተደስተዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዝቋላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዘነቡ ፈንታዬ፤ ሁለቱም ዓይናቸው ማየት ካቆሙ ሦስት ዓመታት እንዳለፉ አስታውሰዋል።
በዚህም ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ባገኙት ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና የሁለቱም ዓይኖቻቸው ሙሉ ብርሃን መመለሱን አረጋግጠዋል።
ከሁለት ዓመታት በላይ የዓይን ብርሃናቸውን በማጣታቸው በጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደው መቆየታቸውን የገለፁት ደግሞ የሰሜን ሽዋ ዞን ደብረ ሲና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፈንታዬ ጌታሁን ናቸው።
በሆስፒታሉ በተደረገልኝ ነጻ ሕክምና የሁለቱም ዓይኖቼ ብርሃን መመለሱ በልጆቼ እየተመራሁ መጥቼ በራሴ እያየሁ እንድመለስ ማስቻሉ ደስታን ፈጥሮብኛል ብለዋል።
ለተደረገላቸው ህክምና አመስግነው አገልግሎቱ በቀጣይም ሌሎች የችግሩ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች በማድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከደቡብ ወሎ ዞን ወግዴ ወረዳ ለህክምናው የመጡት አቶ ሀብታሙ ሽፈራው በበኩላቸው በሰው እየተመራሁ መጥቼ ባገኘሁት ሕክምና የዓይን ብርሃኔ ተመልሶ ዳግም ማየት መጀመሬ የመኖር ተስፋዬን አለምልሞልኛል ብለዋል።
በዚህም ዳግም የተወለዱ ያህል ደስታ እንደተሰማቸው ጠቁመው ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ሕክምናውን ለመሞከር እንጂ ብርሃናቸው ይመለሳል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው አስረድተዋል።
በሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊና የዘመቻው አስተባባሪ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው ከጥቅምት 24/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በተሰጠው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ነጻ ሕክምና አንድ ሺህ 730 ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የዓይን ሞራ ግርዶሽ በይበልጥ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ እንደሚከሰት ጠቁመው፤ በወቅቱ ካልታከመ ለዓይነ ስውርነት እንደሚዳርግ ገልጸዋል።
ችግሩን ለማቃለል ሆስፒታሉ "ኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት" ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ሕክምናውን በዘመቻ በመስጠቱ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ያልታከሙ ወገኖችን ለማገዝ አስችሏል ብለዋል።
በደሴ ከተማ የሚገኘው የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለፉት ዓመታት በዘመቻ ብቻ 20 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።