በጉጂ ዞን 520 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን 520 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ ነው
አዶላ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን 520 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ መስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች በድርቅ እና ተያያዥ ምክንያቶች የሚጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቋቋም አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው።
ግንባታ ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የጎጂ ዞን ሲሆን በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተለያየ ጥቅም የሚሰጡ የመስኖ ግድቦች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ወቅት 520 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ መስኖ ግድቦች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ መስኖና አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ገዳ ሸንዶ (ዶ/ር)፤ የግድቦቹ ግንባታ በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከጉጂ ዞን 13 ወረዳዎች አምስቱ ቆላማ እና በተደጋጋሚ ጊዜ በድርቅ የሚጠቁ ዝናብ አጠርና በብዛት የእንስሳት እርባታ የሚካሄድባቸው ናቸው ብለዋል።
የመስኖ ግድቦቹ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው ቦሬ፣ ዋደራ፣ ሰባቦሩና ግርጃ ዝናብ አጠር ወረዳዎች መሆኑን አንስተዋል።
የመስኖ ግድቦቹ ሲጠናቀቁ ከ520 ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ መስኖ የማልማት አቅም ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ግንባታቸውም በአማካይ ከ50 እስከ 92 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
ግድቦቹ ከመስኖ ልማት ባሻገር የቤት እንስሳትንም የመጠጥ ውሀ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ለመስኖ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ457 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ በጀት መመደቡን አስታውቀው የመስኖ ፕሮጀክቶቹን የግንባታ ስራ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡