በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት አመቱ ጥራቱን የጠበቀ 80 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት አመቱ ጥራቱን የጠበቀ 80 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል
ጊምቢ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ወለጋ ዞን በበጀት አመቱ ጥራቱን የጠበቀ 80 ሺህ ቶን የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በምእራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ቡናና ሻይ ልማት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ የቡና ምርት ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።
የቡና ምርቱ ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚሰበሰብ ጠቅሰው አርሶ አደሩ የደረሰ ቀይ የቡና ፍሬ ብቻ በመልቀም ጥራቱን ለመጠበቅ እንዲቻል ለአምራቾቹ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት አመት በዞኑ በቡና ተክል ከተሸፈነው 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተሻለ የቡና ምርት ይሰበሰባል ብለዋል።
ከሚሰበሰበው የቡና ምርትም ከ80 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማእከላዊ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን በላሎ አሳቢ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ጌታሁን ከበደ፣ በወረዳው ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለመሰብሰብ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የወረዳው ቡና አምራች አርሶ አደሮች በምርት ዘመኑ ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ቀይ ቡና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለመሰብሰብ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዘግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከወረዳው ቡና አምራች አርሶ አደሮች መካከል ጌታሁን ጉታታ፣ በየዓመቱ ከ15 እስከ 25 ኩንታል የቡና ምርት እንደሚያገኙ ጠቅሰው ዘንድሮም የነበረው የአየር ሁኔታ ለቡና ምርት አመቺ በመሆኑ ከ20 ኩንታል በላይ የቡና ምርት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።
አርሶ አደር ገመቹ መላኩ በበኩላቸው ዘንድሮ የደረሰ የቡና ምርት ጥራቱን ለመጠበቅ ከግብርና ባለሙያዎች ስልጠና ማገኘታቸውን አንስተዋል።
ከ15 ኩንታል በላይ የቡና ምርት እንደሚያገኙ ጠቅሰው ዘንድሮም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።