ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎትን ለማዘመን የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው - ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ የዜጎችን ጤና አገልግሎት ለማዘመን የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ። 

የጤና ሚኒስቴር የመድሀኒት አቅርቦት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳለጥ "ጤንነቴ" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ አስመርቋል። 

በተጨማሪም "ለበጎ" የተሰኘ የአምቡላንስ ስምሪት ስርዓትና 952 የጤና መረጃ እና ምክር አገልግሎት ነጻ የስልክ ጥሪ ማዕከልን ስራ አስጀምሯል። 


 

ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴ በዚሁ ወቅት፤ በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ ማዳን ላይ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። 

የዜጎችን የጤና አገልግሎት ለማዘመን የተከናወኑ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረጉት መተግበሪያዎችም ዜጎች ቀልጣፋ፣ ፍትሀዊና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

በራስ አቅም የበለጸጉት እነዚህ መተግበሪያዎች የጤና ስርዓቱን በጉልህ የሚያግዙ መሆናቸውን አንስተው፤ በጤና ስርዓቱ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ የጤናውን ዘርፍ ተደራሽና ቀልጣፋ ለማድረግ ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

ሚኒስቴሩ የዜጎችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በዛሬው ዕለት ወደ ስራ የገቡት መተግበሪያዎች የዚሁ አካል ናቸው ብለዋል። 


 

"ጤንነቴ" የተሰኘው መተግበሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ህብረተሰቡ መድሀኒቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ የለማ መሆኑን ተናግረዋል። 

"ለበጎ" የተሰኘው የአምቡላንስ ስምሪት ስርዓት እና 952 ነጻ የስልክ ጥሪ ማዕከል ለድንገተኛ የጤና አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አንስተዋል። 

በዛሬው እለት የተመረቁት መተግበሪያዎች በአጠቃላይ የጤናውን ስርዓት የሚያሻግሩ መሆናቸውን በመጠቆም።


 

በመርሀ ግብሩ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀስላሴን ጨምሮ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ ቢልለኔ ስዩም እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም