ቀጥታ፡

ከማዕከሉ የምናገኛቸው የሰብል ዝርያዎች ድርቅና ተባይን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ናቸው-የባምባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች 

አሶሳ፤፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ከአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚያገኟቸው የሰብል ዝርያዎች ድርቅና ተባይን በመቋቋም የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባምባሲ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ማዕከሉ በምርምር አውጥቶ በአርሶ አደሮች ማሳ ለማስተዋወቅ ያለማው "BH-520" (ናዳ) የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ በአርሶ አደሮችና በግብርና ባለሙያዎች ተጎብኝቷል። 


 

በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት፤ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በየጊዜው የሚያመጣቸው የሰብል ዝርያዎች ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከአርሶ አደሮቹ መካከል በባምባሲ ወረዳ መንደር 47 ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሀይሉ በየነ እና የሺብር ዘገዬ በቀበሌያቸው እየለማ የሚገኘው አዲስ የበቆሎ ዝርያ ዝናብ እና ተባይን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ማዕከሉ አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን በየጊዜው ከሚያፈልቃቸው ምርጥ ዘሮች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውሰዋል። 

የአሁኑ የመስክ  ጉብኝትም  ማዕከሉ ምርታማነታቸውን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ ላለው ስራ ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታቸው ያዩት የበቆሎ ዝርያ በጥሩ ቁመና ላይ መገኘቱ የተሻለ ዝርያ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑንም ተናግረዋል።

አርሶ አደር መሳይ አበባው በበኩላቸው፤ የምርምር ማዕከሉ በትንሽ ማሳ ላይ ብዙ ምርት መስጠት የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በማፍለቅ ማስተዋወቁን ጠቁመዋል።


 

ከዚህ በፊትም ማዕከሉ ያወጣቸውን አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በመጠቀም በግብርና ሥራቸው ላይ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አክለዋል።

በአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪና የዘርፉ አስተባባሪ ፍቃዱ ቤኛ ማዕከሉ ለአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ የሆኑ አዳዲስ  የምርምር ስራዎችን  በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

ከበቆሎ በተጨማሪ በሰሊጥ፣ ቦለቄ እና ማሽላ ላይ በስፋት የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የምርምር ውጤቱን በማስፋት አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

በወረዳው መንደር 48 ቀበሌ በምርምር ያወጣውና በሄክታር 95 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል "BH-520" (ናዳ) ዝርያም የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።

የምርምር ማዕከሉ የሚያወጣቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የዘር ብዜት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ አቡን ናቸው።


 

አርሶ  አደሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ተጠቅሞ በኩታ ገጠም እርሻ ልማት ውጤታማ የግብርና ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም