ቀጥታ፡

በአዋሽ ወንዝ ከልማት ውጪ የነበረን ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ ልማት ማስገባት ተችሏል

አዳማ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ በአዋሽ ወንዝ ከልማት ውጪ የነበረን ከ70ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ ልማት ማስገባት መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለፁ።

በአዋሽ ተፋሰስ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በዘላቂነት ለማስቀረት የተከናወኑ ተግባራት የአዋጭነት ጥናት ግኝት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትና የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በስምጥ ሸለቆና ኦሞ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በተለይም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ላይ ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ በወንዝ ግራና ቀኝ የውሃ መገደቢያ በመስራት የጎርፍ አደጋን የመከላከል ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።

በዚህም ወንዙ ሲሞላ መገደቢያውን አልፎ በመውጣት አደጋ ሲያደርስ የነበረውን ጎርፍ በመከላከል 70ሺህ 140 ሄክታር መሬት ወደ ልማት እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ከ129 ሺህ በላይ የሚሆን የህብረተሰብ ክፍልን ከመፈናቀል አደጋ መታደግ ተችሏል ብለዋል።


 

የአዋጭነት ጥናቱ ዓላማ የአዋሽ ወንዝን በዘላቂነት ከስጋት ነፃ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ለማስገባትና ወንዙን በሚፈለገው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻል ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

በወንዙ ግራና ቀኝ በተሰራው የጎርፍ መከላከል ሥራ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማረጋገጥ ባለፈ የአደጋ ስጋትና ተጋላጭነትን መቀነስ መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም