ቀጥታ፡

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 1/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ልማትን ለማስቀጠል ብሎም ቀጣናዊ ሚናን ለማጉላት ወሳኝ ሚና እንዳለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ብዙአየሁ ደገፋ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ (ጂኦግራፊያዊ) እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል። 

የቀይ ባሕር ባለቤትነትን ጥያቄ ለመፍታት የተረጋጋ፣ የሰከነና በውይይት ላይ የተመሰረተ አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ ለማጣት የፈጀውን ያህል ለመመለስ አይፈጅም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድም ሕጋዊና ተቋማዊ መሠረት የሌለው የሚያስቆጭ የብሔራዊ ጥቅም ስብራት አካል መሆኑን አስረድተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ብዙአየሁ ደገፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ፣ ሕጋዊና ታሪካዊ ቅቡልነት የሌለው ሴራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሁለንተናዊ እድገትን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ጠቁመው፤ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ብሎም ለሀገር ዕድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሀገራትንና ቀጣናውን እንድትደግፍ የሚያስችላት መሆኑን ጠቁመው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብርና የኃይል ልማት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የቀጣናውን ሀገራት አብሮ የማደግ ዕድል የሚያሰፋ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም