ቀጥታ፡

ቀኑ ወንድማማችነትንና ብዝኀነትን በሚያጠናክር መልክ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 1/2018(ኢዜአ)፡- የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ወንድማማችነትና ብዝኀነትን በይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር ምክር ቤቱ አስታወቀ።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ይከበራል።

የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተሾመ ለምጃቦ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቀኑ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንደሚከበርና በክልል ደረጃ በሳጃ ከተማ ሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ይኖራል ብለዋል።

በዚህም መሠረት ቀኑን ምክንያት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በሕገ-መንግሥትና የፌደራሊዝም አስተምኅሮ ሥርፀት ላይ በየደረጃው ሥልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የደም ልገሳ፣ ዐቅመ ደካሞችን ማገዝና ለዐቅመ ደካማ ወላጆች ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብን ጨምሮ ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ በወልቂጤ ከተማ ባዛርና ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በዓሉን ለሚታደሙ እንግዶች ምቹ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ቀኑ ወንድማማችነትን እና ብዝኀነትን በይበልጥ የምናጎለብትበት ነው ብለዋል።

የቀኑ መከበር የአካባቢውን ቱሪዝም፣ ባህል እንዲሁም ልማት ለማስተዋወቅና የልማት ሥራዎችን በይበልጥ ለማከናወን ከፍተኛ መነሳሳት መፍጠሩንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም