ቀጥታ፡

የተሰጠንን ተልዕኮና ግዳጅ በላቀ ብቃት ለመፈፀም ተዘጋጅተናል-  የምስራቅ ዕዝ ተመራቂ ወታደሮች

ጅግጅጋ፤ ህዳር 1/2018 (ኢዜአ)፡-  የተሰጣቸውን  ተልዕኮ እና ግዳጅ በላቀ ብቃት በመፈፀም  የሀገር  ሉዓላዊነትና  የሕዝብን ደህንነት ለማስከበር  ዝግጁ  መሆናቸውን  በመከላከያ  የምሥራቅ ዕዝ ተመራቂ ወታደሮች  ተናገሩ። 

የምስራቅ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከዕዙ የተለያዩ ኮሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና የሰጣቸውን ወታደሮች ማስመረቁ ይታወሳል።


 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራቂ ወታደሮች፤ ተልዕኳቸውንና ግዳጃቸውን በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈፀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ወታደር ተመስገን በቀለ ለሀገሬና ለሕዝቤ ልዩ ፍቅር አለኝ፤ በዚህም በታማኝነትና በቁርጠኝነት በማገልገል የበኩሌን እወጣለሁ ሲል ገልጿል።


 

በስልጠናው ጠንካራ አቅም ፈጥረናል ያለው ወታደር ተመስገን፤ በማንኛውም መልኩ የሚሰጠውን ሀገራዊ ግዳጅ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛና ዝግጁ  መሆኑን አስታውቋል።

ስልጠናው የአካል ብቃትና የውጊያ ስልቶችን ጨምሮ  የተለያዩ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት አቅሙን ይበልጥ ያጠናከረና  ግዳጆችን በብቃት መወጣት የሚያስችል መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወታደር ካሳዬ ትዕግስቱ ነው።


 

በተለይም የሀገሪቱንና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚነሱ ባንዳንዎች፣ ጽንፈኞችንና ተላላኪዎችን ለመደምሰስ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ስልጠናው በአቅምና በስነ ልቦና እንዲሁም ዘመናዊ የውጊያ ስልትን በአግባቡ የቀሰምንበት ነው ያለው ደግሞ ወታደር ኦልያድ በቀለ ነው።


 

ከአያቶቻችን የወረስነውን ጀግንነት በመላበስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ደህንነት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል  የማስከበር  ግዳጅና ተልዕኮን ለመወጣት ተዘጋጅቻለው ሲል  ገልጿል።

በማዕከሉ አሰልጣኝ ከሆኑት መካከል ምክትል መቶ አለቃ ጅሬኛ ጌታሁን በበኩላቸው፤  ወታደሮቹ በኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውንም ትንኮሳ  መመከት የሚያስችል አቅም  እንደገነቡ ተናግረዋል። 


 

በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ግዳጅ በላቀ ጀግንነት እና የዓላማ ፅናት ለመፈፀም ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው ምክትል መቶ አለቃ ጅሬኛ ያረጋገጡት። 

የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ ፤  ሰልጣኝ የሰራዊቱ አባላት በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለሚሰጣቸው ግዳጅ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የተሟላ የዝግጁነት ቁመና የገነቡ መሆናቸውን በምረቃው ወቅት አረጋግጠዋል።


 

የሰራዊቱ አባላትም በማዕከሉ ያገኙትን ክህሎት በመጠቀም ሕገ መንግስታዊና ተቋማዊ ተልዕኮን በጀግንነት ታጥቀውና ሕዝባዊ ባሕሪ ተላብሰው መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዘበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም