ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው አህጉራዊ የመሬት ፖሊሲ ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ):- ስድስተኛው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኮንፍረንስ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

“የመሬት አስተዳደር፣ ፍትህ እና ካሳ ለአፍሪካውያንና ለዘርዓ አፍሪካውያን” በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚካሄደው ኮንፍረንስ መሪ ሀሳብ ነው።

የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ኮንፍረንሱን በጋራ አዘጋጅተውታል።

ከአፍሪካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና የአካባቢ ጉዳዮች ጋር የተጣጣሙና ለነባራዊ እውነታዎች ምላሽ የሚሰጡ የመሬት ፖሊሲ ምርጥ ተሞክሮዎች በኮንፍረንሱ ይቀርባሉ።

ውጤታማ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመሬት አስተዳደር ስርዓት መገንባት፣ ተቋማዊ አቅምን መፍጠርና ቁጥጥርና ክትትልን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባርነት፣ የቅኝ ግዛት ዘመን መሬት የመንጠቅ ተግባርና በዘር ምክንያት መሬት ከማግኘት መገለል በአፍሪካውያንና ትውልደ አፍሪካውያን የመሬት መብቶች፣ ሀብት አጠቃቀምና እኩልነት ላይ ያሳደራቸውን አሉታዊ ተጽእኖዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይቶች ይካሄዳሉ።

በመሬት አስተዳደር፣ ፍትህ እና ካሳ ያሉ ውይይቶች ማጠናከር እና ፖሊሲ ተኮር ምላሾችን መስጠት ሌላኛው የኮንፍረንሱ አላማ ነው።

የስርዓተ ጾታ እኩልነት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ቴክኖሎጂዎችን ከመሬት ፖሊሲ እና አስተዳደር ጋር ማስተሳሰር ትኩረት ተሰጥቶታል።

በኮንፍረንሱ የመሬት ፖሊሲ፣ የመሬት ፍትህ፣ የማካካሻ ፍትህ እና የመሬት ባለቤትነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ፣ የህግ እና ተቋማዊ ምክረ ሀሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአህጉራዊ ኮንፍረንሱ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት፣ የህብረቱ ተቋማትና አደረጃጀቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ተመራማሪዎች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ ትውልደ አፍሪካውያንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።

ኮንፍረንሱ እስከ ህዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኮንፍረንስ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሁነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም