ቀጥታ፡

የኮፕ 30 አጀንዳዎች እና የኢትዮጵያ ተሳትፎ

30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 30) ዛሬ ይጀምሯል። “የአየር ንብረት እርምጃ እና ትግበራ” የጉባኤው ዋና መሪ ሀሳብ ነው።

ከኮፕ 30 ቁልፍ ግቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

  • የኢነርጂ፣ ኢንዱስትሪ እና ትራንስፖርት ስርዓቶችን ሽግግር ማፋጠን። በዚህም የታዳሽ ኃይልን በሶስት እጥፍ መጨመር፣ የኢነርጂ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ማረጋገጥና የበካይ ጋዞችን በጊዜ ሂደት መጠቀም ማቆም መቀነስ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ይካሄዳሉ።
  • ተፈጥሮን፣ ደኖችን፣ ውቅያኖሶችን የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን መጠበቅና ወደ ቀደመ ይዞታቸው መመለስ፣ የደን ጭፍጨፋን ማስቆም እና የተጎዱ ስነ ምህዳሮች ዳግም እንዲያገግሙ ማድረግ
  • ግብርና እና ስርዓተ ምግብን መቀየር፤ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም፣ የማይበገር ስርዓተ ምግብ መገንባትና የምግብና የስነ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ።
  • ለከተሞች፣ ለመሰረተ ልማቶችና ለውሃ ስርዓቶች የማይበገር አቅም መገንባት፣ የሰው ኃይልና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች አቅሞችን መጠቀም።
  • የንግድ ማህበረሰቦች፣ ከተሞች፣ ባለሀብቶችና የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማትን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በኮፕ 30 የተግባር አጀንዳ አማካኝነት በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ይገኙበታል።


 

ከተጠቀሱት ግቦች የተለያዩ ውጤቶችም ይጠበቃሉ።  

  1. የኮፕ 30 የተግባር አጀንዳ የሚያስፈጽም የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀት፣ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ወደ ተግባር መለወጥና ተግበራዊነቱን የሚቆጣጠሩ ቡድኖች ከጉባኤው በኋላ እንደሚቋቋሙ ይጠበቃል።
  2. ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት የፋይናንስ ግብን ማጠናከር ሌላኛው አጀንዳ ሲሆን የበለጸጉ ሀገራት በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ቃል የገቧቸውን የገንዘብ ድጋፎች እንዲሰጡ ጠንካራ ጥሪ ይቀርባል።
  3. የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህ፣ ፍትሃዊ የኢነርጂ ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት፣ አቅም ግንባታና  ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅ ውጤት ነው።

መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ማሳደግና የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር ትኩረት የተሰጠሰው ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።

ለአፍሪካ ኮፕ 30 ለአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዋ መፍትሄ የሚያመጡ ውሳኔዎችን የምትጠብቅበት መድረክም ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ተደራሽነት ማሳደግና ፍትሃዊነትን ማስፈን፣ ፍትሃዊ የኢነርጂና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ፣ ተፈጥሯዊ መፍትሄዎች፣ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ፣ ኢኖቬሽን፣ የማይበገር አቅምን መገንባትና የዜጎች መብት ጥበቃ ከአፍሪካ አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ዝቅተኛ ድርሻ ቢኖራትም ዋነኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ናት። ተከታታይ ድርቆች፣ ጎርፎችና በረሃማነት አበይት ፈተናዎቿ ናቸው። በዚህ ረገድ ኮፕ 30 ለአፍሪካ በማይበገር አቅም ግንባታ፣ መሰረተ ልማት አቅርቦትና የኢነርጂ ተደራሽነት ላይ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ይጠበቃሉ።

የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ጉዳይ በኮፕ 30 ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አፍሪካውያን ይሻሉ። ኮፕ 30 ለአፍሪካ የትርክት ሽግግር የምታደርግበት ነው ማለት ይቻላል። አፍሪካ የችግሩ ተጎጂ ነኝ ከማለት ባለፈ ታዳሽ ኢነርጂ፣ የካርቦን ገበያና አረንጓዴ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ መፍትሄዎችን አፍላቂ አህጉር መሆኗን በግልጽ የምታሳይበትና ለዓለም ድምጿን የምታሰማበትም ነው።


 

13ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥና ልማት ጉባኤ ’’በሳይንስ፣ በገንዘብና በፍትሐዊ ሽግግር የአፍሪካን የአየር ንብረት እርምጃ ማንቃት” በሚል መሪ ሃሳብ በነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

በጉባኤው ላይ የተሳተፈው የአፍሪካ የአየር ንብረት ድርድር ቡድን በብራዚል በሚካሄደው ኮፕ-30 የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ የአፍሪካን ቀዳሚ የልማት አጀንዳዎች የሚያንጸባርቁ የድርድር ሃሳቦችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል።

በጉባኤው የአፍሪካን የልማት መሻት ያነገቡ የተቀናጁ፣ ወጥነትና ጥራት ያላቸው የድርድር ሀሳቦች ለማቅረብ ዝግጅት እንደተደረገ አመልክቷል። የአፍሪካን የልማት ጸጋዎች የዓለም አቀፍ የመፍትሔ ለማድረግ በአዲስ አስተሳሰብ በመተባበር ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ቡድኑ ገልጿል።

አፍሪካ በ2030 የአየር ንብረት ግቦቿን ለማሳካት ከሚያስፈልጋትና ቃል ከተገባው ውስጥ ከ3 እስከ 4 በመቶ የማይበልጥ የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገላት መሆኑን መረጃዎች ያመክታሉ። ተደራዳሪ ቡድኑ በብራዚል ቤሌም ከተማ በሚካሄደው ኮፕ-30 ጉባኤ ላይ የአፍሪካን የፋይናንስ ፍትሐዊ አጀንዳ በአንድ አህጉራዊ ድምጽ ማሰማት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በኮፕ 30 በአፍሪካ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ የመሪነት ሚናዋን ለመወጣት ተዘጋጅታለች። 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 30) የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት ወሳኝ ምዕራፍ ሊሆን እንደሚገባም ደጋግማ ገልጻለች።

በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ኢትዮጵያ  ማንንም ሳትጠብቅ ተጨባጭ እርምጃ ወስዳለች። አረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ግብርናውን ጨምሮ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የታገዙ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እርምጃዎች እየሰወደች ነው።

ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 . በአዲስ አበባ የአፍሪካን የጋራ ድምጽ የያዘውን የአዲስ አበባ ድንጋጌ በማጽደቅ መጠናቀቁ ይታወሳል።

የአየር ንብረት ጉባኤውን በጋራ ያዘጋጁት ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ህብረት የጣምራ መግለጫ ማውጣታቸውም አይዘነጋም።

በጉባኤው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ቃል መገባታቸውንና ታሪካዊው የአዲስ አበባ ድንጋጌ መጽደቁን ገልጾ፥ ይህም የአፍሪካ መሪዎች በዓለም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጿል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት Africa Climate Innovation Compact እና African Climate Facility የተሰኙ ኢኒሼቲቮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች 50 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በየዓመቱ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል።

መሪዎቹ በጉባኤው ላይ የአፍሪካአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጸው የጋራ መግለጫው፥ ፈንዱ እዳን ከሚያሸክሙ ብድሮች ይልቅ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁሟል። በጉባኤው ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ ኢምፖርት እና ኤክስፖርት ባንክ(አፍሪኤግዚም ባንክ) አፍሪካ 50 የተሰኘ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ማዕቀፍን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአፍሪካ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ኢኒሼቲቭ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ሌሎች ሀገር በቀል የአየር ንብረት ፕሮጀክቶችን የሚደግፉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ይፋ ሆነዋል።

መሪዎች በጉባኤው አፍሪካ .. 2030 በዓለም የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ያላትን ድርሻ 2 በመቶ ወደ 20 በመቶ ከፍ ለማድረግም ቃል ገብተዋል። የአረንጓዴ ማዕድናት እና ንጹህ የኢነርጂ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስትራቴጂዎችን ማጠናከር ሌላኛው ጉባኤው ከስምመነት ላይ የደረሰበት አጀንዳ ነው።

አፍሪካ በብራዚል ቤለም የሚካሄደውን (ኮፕ 30) የፀደቀውን የአዲስ አበባ ድንጋጌ አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጸና መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ኮፕ 30 ከዓለም የአየር ንብረት አስተዳደር አንጻር ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን ቃል ኪዳኖቹ ወደ ተጨበጡ ውጤቶችና የተግባር እርምጃዎች የሚቀየሩበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በጉባኤው የተገቡ ቃሎችና ትግበራን የሚያስታርቅ ነው ያሉትም አልጠፉም።

በአጠቃላይ ጉባኤው ሁሉን አካታችና ተግባር ተኮር የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚስተጋባበትና አስቸኳይ ጥሪ የሚቀርበበት ነው። አፍሪካም በጋራ ድምጿን ከማሰማት ባለፈ ፍትህና የተግባር ምላሽን የምትጠብቅበት ነው። ቃልን ወደ ተግባር መለወጥ የሚጨበጥ ለውጥ በማምጣት መጻኢ ጊዜ ፍትሃዊ እና ዘላቂነትን ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን ያስችላል።

30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 30) እስከ ህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም