ቀጥታ፡

መቻል እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር መቻል እና ፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ማምሻውን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተደርጓል።

ሁለቱ ቡድኖች በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ከሲዳማ ቡና የመረከብ እድላቸውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በሌላ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ  እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ያሬድ ብሩክ ለሃዋሳ ከተማ፣ አዲስ ግደይ ለንግድ ባንክ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሸገር ከተማ በተመሳሳይ አንድ አቻ ወጥተዋል።

ብሩክ በየነ ለሀዲያ ሆሳዕና፣ ሄኖክ አዱኛ በፍጹም ቅጣት ምት ለሸገር ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ቀን ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ሌላኛው  ጨዋታ አዳማ ከተማ በነቢል ኑሪ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።

የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር በኋላ ከህዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተደርገዋል።

ይርጋጨፌ ቡና እና አዳማ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። መንደሪን ክንድሁን ለይርጋጨፌ፣ አህላም ሲራጅ ለአዳማ ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም