በደብረ ማርቆስ ከተማ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ አባላት እውቅናና የማእረግ እድገት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ማርቆስ ከተማ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ አባላት እውቅናና የማእረግ እድገት ተሰጠ
ደብረ ማርቆስ ፤ጥቅምት 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ተግባር የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አባላቱ እውቅናና የማእረግ እድገት ሰጠ ።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ተግባር የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አባላቱ ዛሬ እውቅናና የማእረግ እድገት ሰጥቷል ።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ የመደበኛና አድማ መከላከል ፖሊስ አባላት እውቅናና የማእረግ እድገት ተሰጥቷል ።
የፖሊስ አባላቱ በተለይም ባለፉት አመታት በተከናወነ የተቀናጀ የሰላምና የጸጥታ እንዲሁም የህግ ማስከበር ተግባር የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተወካይ አቶ መኮንን ሙሉአዳም በበኩላቸው ፖሊስ በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ባደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል ።
የከተማው ፖሊስ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ባከናወነው የጸጥታና የህግ ማከበር ተግባር በከተማውና አካባቢው አሁን ለሰፈነው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የተገኘው ሰላም በዘላቂነት እንዲቀጥል የትብብር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
በከተማው ዛሬ እውቅናና የማእረግ እድገት ከተሰጣቸው የፖሊስ አባላት መካከል የከተማ አስተዳደሩ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ኢንስፔክተር ብሩክ ሁነኛው በበኩላቸው የተጣለባቸውን ተልእኮ ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የተሰጣቸው እውቅናና የማእረግ እድገት ለቀጣይ ተልእኮ የበለጠ እንደሚያነሳሳቸው አመላክተዋል ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ602ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ሶፍያ መሀመድ በስነ ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት በአካባቢው የሚከናወነው የህግ ማስከበር ስራ የሀገርንና የህዝብን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ያለመ ነው።
ከፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።