ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን በተቀናጀ መንገድ የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ቢሮው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለፀ።

የድሬዳዋ አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን በበኩሉ ውብና ፅዱ ከተማን በመፍጠር ጤናማ ማህበረሰብ የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እንደገለፁት፤ የክረምት ወራት ማለፉን ተከትሎ በትንኝ ንክሻ የሚተላለፉ ወባ፣ ደንጊ እና ቹኩንጉኒያ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን በተቀናጀ መንገድ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው።

ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የወባ መራቢያ ስፍራዎችን የማዳፈን፣ የማድረቅና አካባቢን የማፅዳት ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በተመረጡ ስፍራዎች ደግሞ ፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት በመከናወኑ አበረታች ለውጦች ተገኝተዋል ብለዋል።

የመከላከሉ ሥራ በዘመቻ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ማህበረሰቡን በማስተማርና በወባ በሽታ ለታመሙ አስፈላጊውን ህክምና በመስጠት የበሽታውን ስርጭት ለማቆም እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርና በከተማ ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትን በማረጋገጥ በህክምናው ሆነ በመከላከሉ ረገድ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ዶክተር ፅጌረዳ ተናግረዋል።

የአስተዳደሩ አካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አብዶ መሐመድ በበኩላቸው ፅዱና ወብ ድሬዳዋን በመገንባት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለወባና ተላላፊ በሽታዎች መንስኤ የሆነውን ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲወገድ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም በውሃማ አካባቢዎች በዘፈቀደ የሚጣሉ ቆሻሻዎች ለትንኝ መራቢያ መንስኤ በመሆናቸው ችግሩን ከጤና ቢሮ፣ ከፅዳትና ውበት ኤጀንሲ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰራቱ የተሻለ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን አስረድተዋል።

እየተከናወነ በሚገኘው ሀገር አቀፍ የፅዱ ኢትዮጵያ ዘመቻም በድሬዳዋ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመስራቱ ህብረተሰቡ ፅዱና ውብ ድሬዳዋ ለመፍጠር ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

ባለስልጣኑ አካባቢን በሚበክሉ፣ ለተላላፊ በሽታዎች ህብረተሰቡን እያጋለጡ በሚገኙ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳዳግ ሥራ ከተጠናከረ እና ነዋሪው ቤቱንና አካባቢውን የማፅዳት ባህሉን ካጠናከረ ፅዱ ድሬዳዋ እና ጤናማ ህብረተሰብ የመፍጠሩ ጉዞው የበለጠ ስኬታማ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም