ቀጥታ፡

መንግሥት ለያዘው የማዕድን ልማት መጠናከር ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር ሊደግፉ እንደሚገባ ተመላከተ

አዳማ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት የማዕድን ልማትን ለማጠናከር የሰጠው ትኩረት ለሀገራዊ ዕድገት መፋጠን ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በጥናትና ምርምር መደገፍ እንደሚገባ በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርቲው የተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ የአፕላይድ ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊና ተመራማሪ አስፋው ኤርበሎ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት የማዕድን ልማትን እንደ አንድ ዋነኛ የዕድገት ምንጭ አድርጎ መንቀሳቀሱ የሚደገፍ ነው።

ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማጠናከር በሚሰራው ሥራ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።

የማዕድን ልማት በተፈጥሮ ውስብስብ ሂደቶች እንዳሉትና ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ይህንንም ለመፍታት በየጊዜው ጥናትና ምርምር ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ ለማዕድን ልማቱ ስኬታማነት የራሳችንን አስተዋጽኦ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጠንካራ ቤተ ሙከራ በማደራጀት ዘርፉን የሚያሳድጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማካሄድ መንግስትን ማገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ምህዳር ሣይንስ ክፍል የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በዘመናዊ ላቦራቶሪ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነት የኤሌክትሪክ መኪናዎች እንዲሁም በውሃና በንፋስ ኃይል የሚሰሩ የሃይል ማመንጫ ማሽነሪዎች የሚሰሩት ማዕድናትን በመጠቀም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎችና መምህራን መንግሥት ለያዘው የማዕድን ልማት ግብዓት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍልም በአዳማ ከተማ ዙሪያ ባሉ የማዕድን አይነቶች ላይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጥናትና ምርምር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይ ከአዳማ ከተማ ዕድገት ጋር ተያይዞ በአካባቢው ከፍተኛ የግንባታ ግብዓት ፍላጎት እንዳለ የጠቀሱት ኃላፊው፣ ይህንን ፍላጎት ለማርካትና ሀብቱን በሥርዓት ለማስተዳደር ጥናቱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሰቲው የማዕድን ኢንጂነሪንግ ጂኦፊዚክስ መምህር አብደላ በሪሶ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያላቸውን የሥነ ምድር ሳይንስ ምሁራንና ተመራማሪዎችን ከማፍራት ጎን ለጎን እንደሀገር ትኩረት ለተሰጠው የማዕድን ልማት አጋዥ ለሆኑ ጥናትና ምርምሮች ትኩረት ሰጥቷል።

መንግሥት በማዕድን ዘርፍ የያዘው አቅጣጫ የሀገሪቱን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ወሳኝ በመሆኑ ምሁራን ሙያዊ አስተዋጽኦ በማድረግ ልንደግፍ ይገባል ብለዋል።

የማዕድን ልማት በባህሪው ሰፊ ሀብትና እውቀት የሚጠይቅ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም