ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች ቁጥር እንዲጨምር አግዟል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎችን ቁጥር በመጨመር በደመቀና በምቹ ሁኔታ እንዲካሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ገለጸ።

በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር የገዘፈ ስም ባለው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ በ1994 ዓ.ም የተመሰረተው ታላቁ ሩጫ፤ እስከ 2017  ዓ.ም ድረስ በድምሩ ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን ማስተናገዱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የመጀመሪያው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ያነሱ ተሳታፊዎች የነበሩት ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት ውድድሩ 50 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል።

በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሆነ የሚነገርለት ውድድር፤ ከኢትዮጵያውን ባሻገር ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች የሚመጡ የውጪ አገራት ዜጎችም የሚሳተፉበት ሆኗል።

በተለያያ ወቅት የዓለም ታላላቅ አትሌቶች ውድድሩን በክብር እንግድነት በማስጀመር የተሳተፉ ሲሆን፤ ለአብነትም ፖል ቴርጋት፣ ገብርኤል ዛቦ፣ ካሮሊና ክሉፍት ፣ ዴቭ ሞርክሩፍት እና ፓውላ ራድክሊፍ ይጠቀሳሉ፡፡

በውድድሩ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ስለሺ ስህን፣ ጸጋዬ ከበደ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔና ጥሩነሽ ዲባባ ማሸናፋቸው ይታወሳል፡፡

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተተኪ አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ ኢትዮጵያ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደምትችል እያሳየ ይገኛል።

በየዓመቱ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ውድድር የኢትዮጵያን ገጽታ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያነሳው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ፤ በተለይ የኮሪደር ልማቱ ውድድሩ ያማረና የደመቀ እንዲሆን ማድረጉን  ተናግሯል።


 

የታላቁ ሩጫ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ በበኩሉ፤ የኮሪደር ልማቱ የውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ተናግሯል።

አብዛኛዎቹ የከተማዋ መንገዶች ከኮሪደር ልማቱ በፊት ለእግረኞች የተለየ መሄጃ የሌላቸውና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ እንዳልነበሩ አስታውሷል፤ በዚህም ለተወዳዳሪዎች ደህንነት ሲባል በየዓመቱ የተሳታፊዎችን ቁጥር በአንድ ሺህ ወይም በሁለት ሺህ ብቻ ለመጨመር ተገደው መቆየታቸውን አስታውቋል።


 

የኮሪደር ልማቱ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በተለይም የመሮጥ ባህልን ለማስፋፋት እና ሰፊ ህዝብ የሚሳተፍባቸውን  ውድድሮች ለማዘጋጀት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጿል። 

የኮሪደር ልማቱ ለስፖርቱ የሚያገለግሉ መንገዶችን በመያዙ የታላቁ ሩጫ ውድድር ተሳታፊዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እንዳስቻለ ተናግሯል።

ይህን ተከትሎ በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መርኃ ግብር 55 ሺህ ተሳታፊዎች እንደሚወዳደሩ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም