ቀጥታ፡

ኤሌክትሪክ እንዳይቋረጥና ሲቋረጥም ፈጣን መረጃ የሚሰጥ "ስካዳ" የተሰኘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ ኤሌክትሪክ እንዳይቋረጥና ሲቋረጥም ፈጣን መረጃ በመስጠት የሃይል ተደራሽነትን ማስፋት የሚያስችል "ስካዳ" የተሰኘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና የኢንዱስትሪ ልማትን በማስፋፋት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡

የለውጡ መንግስት አዳዲስ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ ብዝኃ የሀይል ማመንጫዎችን በማስፋትና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን መልሶ ግንባታና በአዲስ በመተካትና የትራንስፎርመሮችን አቅም በማሳደግ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱን ከዚህ በላይ ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የአራት ሺህ ትራንስፎርመሮችን አቅም ማሳደግ እና ከ625 ኪሎ ሜትር በላይ ያረጁ መስመሮችንና ፖሎችን በአዲስ መቀየራቸውን ጠቅሰው፤ በክልሎችም ተመሳሳይ ሥራ በማከናወን የሀገሪቷ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን 54 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመትም ለ800 ሺህ ደንበኞች ቆጣሪ ለማሰራጨት እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዜጎችን ፍትሐዊ የሀይል ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር እየተጠቀመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በዚህም አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችል ዘመኑን የዋጅ "ስካዳ" የተሰኘ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ስካዳ" በየትኛውም ቦታ የኤሌትሪክ ሃይል ሲቋረጥና ከመቋረጡ በፊት ቢሮ ውስጥ ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸው፤ የትኛው መስመር የትኛው ቦታ ላይ እንደተበላሸ ለማወቅ ያግዛል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የኤሌትሪክ ሃይል እንዳይቆራረጥ ቀድሞ መረጃ በማጋራት ደንበኞች ከመደወላቸው በፊት ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የ"ስካዳ" ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋና ጅማ ተግባራዊ መሆኑን አመልክተው፤ በአዲስ አበባ ከተማም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሚተገበር ተናግረዋል። 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም