ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት የስራ መመሪያ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት የስራ መመሪያ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የፓርቲው ፕሬዚዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት የስራ መመሪያ ተጠናቋል።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋናው ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ እንዳስታወቁት "በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከጥቅምት 19 እስከ 30 በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት የስራ መመሪያ ዛሬ በስኬት ፍፃሜውን አግኝቷል ብለዋል።
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወደ 2000 የሚጠጉ የፓርቲያችን አመራሮች የተሳተፉበትና የአስተሳሰብ አንድነት ከመፍጠርና የተግባር አፈፃፀምን ከማላቅ አኳያ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ በተገኘበት በዚህ ስልጠና ፓርቲያችን እውነተኛ የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት መሆኑም በተጨባጭ የተንፀባረቀበት ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ የስልጠና መርሀ ግብር ከዝግጅት እስከ ገለፃ፣ የቡድን ውይይት፣ ተሞክሮ ልውውጥ፣ የልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት እና ማጠቃለያ ድረስ ዓላማውን በሚገባ አሳክቶ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችሁን ለተወጣችሁ አስተባባሪዎች፣ አሰልጣኞች፣ አወያዮች፣ የፀጥታ ተቋማት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ልዩ ልዩ ተቋማቱ፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች በሙሉ ላበረከታችሁት ከፍተኛ አስተዋፅዖ በብልፅግና ፓርቲ ስም ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው።