ማዕከሉ ለአርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ ለአርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው
አሶሳ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የምርምር ማዕከሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባምባሲ ወረዳ በምርምር ያወጣውን "BH520"(ናዳ) የተሰኘ የበቆሎ ዝርያ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።
የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ደስታ በቀለ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ላይ ውጤታማ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በማሽላ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎች ያወጣቸው አዳዲስ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
በባምባሲ ወረዳ አራት ሄክታር ማሳ ላይ እየለማ የሚገኘው "BH520"(ናዳ) የበቆሎ ዝርያ በሄክታር እስከ 95 ኩንታል ምርት የሚሰጥና አረምና ተባይን የመቋቋም አቅም ያለው ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አዲስ የተለቀቀው የበቆሎ ዝርያ ድርቅን መቋቋም የሚችል፣ በአጭር ጊዜ የሚደርስና ምርታማነቱ የተረጋገጠ የምርምር ውጤት እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
የባምባሲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አብዱልዋሂድ አዙቤር በበኩላቸው፤ የምርምር ማዕከሉ በየጊዜው የሚያወጣቸው አዳዲስ ዝርያዎች አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ከማድረግ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ ዕገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩ ማዕከሉ የሚያወጣቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመተግበር ውጤታማ የግብርና ስራ ማከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በወረዳው መንደር 48 ቀበሌ እየለማ የሚገኘው አዲሱ የበቆሎ ዝርያ የሁሉንም አርሶ አደሮች ትኩረት የሳበ እና በግብርና ስራ ላይ የአርሶ አደሩን ተነሳሽነት የጨመረ ነው ያሉት ደግሞ የባምባሲ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጃፈር አኑር ናቸው።
በመስክ ምልክታው የክልል፣ የዞና እና የወረዳ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።