የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ለመቆጣጠርና የፓርኪንግ ስርዓቱን ምቹ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮች እየተተገበሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ለመቆጣጠርና የፓርኪንግ ስርዓቱን ምቹ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮች እየተተገበሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ ፍሰት ለመቆጣጠርና የፓርኪንግ ስርዓቱን ለአገልግሎት ሰጪዎችና ለተጠቃሚው ምቹ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ አሰራሮች እየተገበሩ መሆኑን የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት የትራንስፖርት ዘርፋን በማዘመን የትራፊክ እንቅስቃሴውን ምቹ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የትራንስፖርት ደንብን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች አማካኝነት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ችግሩን ለመፍታት ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሚበዛባቸውን ስፍራዎች በባለሙያ በማስጠናት የማስተካከያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመዲናዋን የመንገድ ትራንስፖርት ለማሳለጥ በአሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ባለፋት ሶስት ወራት በአዲስ አበባ የትራፊክ ህግን የጣሱና ደንብ የተላለፋ አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
የትራፊክ ማኔጅመንት የስራ ባልደረባ ሆነው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 14 ተቆጣጣሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ጨምረው አስታውቀዋል።
ከፍጥነት ወሰን በላይ እና አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የትራፊክ መብራት መጣስ ዋነኞቹ የደንብ መተላለፍ የተፈጸመባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተቋሙ የቁጥጥርና የፓርኪንግ ስርዓትን ለአገልግሎት ሰጪና ለተጠቃሚው ምቹ ለማድረግና የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ምቹ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፓርኪንግ ክፍያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መፈጸም መጀመሩ ከብልሹ አሰራሮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመቀነስ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።