በክልሉ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቷል
ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ ዘመዴ አንዳርጌ ለኢዜአ እንዳሉት ኅብረተሰቡ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ መንገድ መቆራረጥና መሰል ቅሬታዎችን ሲያነሳ ቆይቷል።
እነዚህን ህገወጥ ተግባራት በማረም ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እንዲቻል ከቢሮ እስከ መናኻሪያ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍትሄው ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ለዚህም በቅድሚያ ተቋምን መገምገምና ማጥራት አስፈላጊ በመሆኑ በየደረጃው ባሉ የሥራ ክፍሎች የግምገማ መድረክ መካሔዱን ጠቅሰዋል።
በዚህም በትራንስፖርት አገልግሎት ሕግ ለማስከበር በሚሰራው ሥራ ክፍተት በሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ከህዳር ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ከተፈቀደ በላይ ሰው በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና በሌሎች በህገ ወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ አሽከርካሪዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃም እንደሚጠናከር ተናግረዋል።
በዘላቂነት ችግሩን እንዲፈታም የትራንስፖርት አገልግሎት መመሪያን ከማሻሻል ባለፈ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።
በተጨማሪም ለአሽከርካሪዎች የተጀመረው በምዘና የተደገፈ የተሐድሶ ሥልጠና እንዲሁም የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል በላይ ከፋ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የቆዩ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል።
ከታሪፍ በላይ ከማስከፈል ባለፈ ለመጫን ከተፈቀደው ሰው በላይ በመጫን ለተሽከርካሪ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ተደራርቦ የሚኬድበት አግባብ እንዳለና ይህንንም በቅንጅት ማረም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ተሳፋሪዎች ጉዳያቸው ላይ መድረስ ስለሚፈልጉ ብቻ ለሕገ ወጥ ተግባራት ተባባሪ እየሆኑ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ኮማንደር አትርሴ የተባሉ ሌላው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው።
መንግሥት ከመናኸሪያ ጀምሮ ተከታታይነት ያለውና ቋሚ የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቶ ከሠራ እንደተሳፋሪ መብታችንን ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንሰራለን፤ ሕጋዊነትንም እናበረታታለን ብለዋል።