ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከ474ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በበጀት አመቱ አራት ወራት ከ474ሺህ በላይ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ ዋስሁን ጎልጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ በክልሉ የሚገኙ ስራ አጥ ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

በዚህም ከስራ አጥ ወጣቶች፣ ከወላጆች፣ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሃደ ሲንቄዎች ጋር የስራ ልየታና አመለካከት ላይ በማተኮር የግንዛቤ ማስረጽ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋርም ሰፊ መውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በበጀት አመቱ ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፤ ባለፉት አራት ወራት ከ474ሺህ በላይ ዜጎች በሀገር ውስጥና በተለያዩ የውጪ ሀገራት የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል 416ሺህ 995 የሚሆኑት በሀገር ውስጥ የስራ ዕድል ተጣቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ 58ሺህ 741 ዜጎች ደግሞ በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸው የብቃት ማረጋገጫ በማግኘት ወደተለያዩ ሀገራት መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በገጠሩ አካባቢ ወደ ስራ ለገቡ ዜጎች በስፋት በግብርና ልማት ኢንሼቲቮች መሳተፋቸውን አንስተው በከተማም ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ተሞክሯል ብለዋል።

የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በኢንቨስትመንት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በአገልግሎት፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በጎጆ እንዱስትሪዎች፣ በብረታብረት፣ በእንጨትና እንጨት ውጤቶች ዘርፍ መሆኑን አብራርተዋል።

እንዲሁም በእንስሳት እርባታ፣ በወተት ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በፍራፍሬና አትክልት ልማት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በሚሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ክህሎት መር ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ስምንት ቢሊዮን ብር ብድር መቅረቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 15ሺህ ሄክታር መሬትና 2ሺህ 500 የማምረቻና መሸጫ ቦታዎች መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በቀጣይም የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም