ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማቱ የድሬዳዋን የቱሪስትና የኢንቨስትመንት መዳረሻነት እያሳደገ ነው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ የኮሪደር ልማት የከተማዋን የቱሪስትና የኢንቨስትመንት መዳረሻነት እያሳደገው መሆኑ ተመለከተ።

የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበትና ገጽታ ከማሳደግ ባለፈ የየከተሞቹን የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻነት እያሳደገው ይገኛል።

ወትሮም በቱሪስት መስህብነቷ የምትታወቀው ድሬደሠዳዋ የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮላታል።


 

በአስተዳደሩ የፕሮጀክት ግንባታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወንድወሰን ጀንበር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ የ11 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት የድሬዳዋን የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻነት አሳድጎታል።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ ከባቡር መስመርና ተርሚናል ጋር ተጣጥሞ መሰራቱ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲሳለጥ ማድረጉን አክለዋል።

የከተማዋን ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች በማሳደግ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማትን በማስቀጠልም ሁለተኛው ዙር የ16 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።


 

በእስካሁኑም ከሳብያን ድልድይ እስከ ነፃ ንግድ ቀጣና ባለው ጎዳና ላይ የእግረኛ፣ የብስክሌትና አካፋይ የአረንጓዴ ልማቶችን ከተቋማት ጋር በመናበብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የሙዚየም እና የባህል ቤቶች ቡድን መሪ ኤርሚያስ ታደሰ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ 130 ዓመታት ካስቆጠረው የባቡር ቅርስ ጋር ተጣጥሞ በመሰራቱ የቱሪስት ፍሰትን በከፍተኛ መጠን ጨምሮታል ብለዋል።


 

በድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ጥናት መረጃ ዝግጅትና ፕሮሞሽን ቡድን አስተባባሪ አበራ መንግስቱ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ለስራ ምቹ በማድረጉ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት።

ለአብነትም በበጀት አመቱ ሩብ አመት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም