በጎንደር ከተማ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን ዳግም ትንሳኤ የሚያበስሩ ናቸው - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን ዳግም ትንሳኤ የሚያበስሩ ናቸው - ነዋሪዎች
ጎንደር፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በመንግስት ልዩ ትኩረት የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን ዳግም ትንሳኤ የሚያበስሩና ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ናቸው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በመገምገም የጥገናና እድሳት ሥራው የተጠናቀቀውን ታሪካዊውን የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ለጉብኝት ክፍት ማደረጋቸው የሚታወስ ነው።
አስተያየተቻውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች የለውጡ መንግስት ሌት ተቀን በመስራት ሀገር የሚለውጡና የሚቀይሩ ትጉህና ታታሪ መሪዎችን በተግባር አሳይቷል ብለዋል፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል መራ አብተው እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት በከተማው የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የስልጣኔ፣ የኪነ ሕንጻና የኪነ ጥበብ ማዕከል የሆነችው ጎንደርን ዳግም ታሪኳን ያደሰ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪክ የተለያዩ መሪዎች ወደ ስልጣን ቢመጡም የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስትን ቅርስ በማደስም ሆነ በመጠገን ከገጠመው የህልውና አደጋ የታደጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ብቻ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ሥራ ታሪክን ከመጥፋት የታደገና የጎንደርንም ዘመናት የዘለቀ ገናና ስምና ታሪክ የሚያስቀጥል ነው ያሉት ደግሞ አድማሴ ደሞዝ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎንደር በዳግም ውልደት ላይ ትገኛለች እንዳሉት ይህን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከዳር በማድረስ ትንሳኤዋን ለማብሰር ከመሪዎቻችን ጎን በመቆም ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
መገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ካጋጠሙት ውስብስብ ችግሮች ተላቆ አሁን ላይ በጥሩ የግንባታ አፈጻጸም ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በህዝብ ተሳትፎ ጭምር እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማውን ገጽታ የቀየረና የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ ፍሰሃ አዳነ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አመራራቸው ለጎንደር ልማትና እድገት የሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ቃልን በተግባር ያሳየ ከመሆኑም በላይ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ ተስፋ ሰጪ ሜጋ ፕሮጀክቶች በአካባቢው በሰፈነው ሰላም የተገኙ እድሎች በመሆናቸው የልማት ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በጎንደር ከተማ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው የቆዩት የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግንባታ እንዲሁም የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ዳግም ሥራቸው እንዲጀመር መደረጉ የሚታወቅ ነው፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማውን ገጽታ ከማሳደግ ባለፈ እድገትን በማፋጠንና ምቹ አካባቢን በመፍጠር ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን በማድረግ በኩል የጎላ ሚና አለው።
ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስትን ከህልውና አደጋ ወጥቶ አሁን ላይ ለትውልድ በሚሻገር መልኩ የእድሳትና ጥገና ሥራው ተጠናቆ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በይፋ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡