የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 7 ሰዓት አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አንድ ግብ ሲያስቆጥር ምንም ጎል አላስተናገደም። አቻ የወጣባቸው ጨዋታዎች ያለ ምንም ግብ የተጠናቀቁ ናቸው።
ቡድኑ በስድስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና እስከ አሁን ባካሄዳቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው እንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦች ተቆጥሮበታል።
ቡናማዎቹ በአራት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ጨዋታው አዳማ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከአራተኛ ሳምንት ሽንፈቱ በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ሸገር ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋሉ።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በአራት ነጥብ 13ኛ፣ ሀዲያ ሆሳዕና በሁለት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሸገር ከተማ በአራተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ እስከ አሁንም ምንጭ ጨዋታ አላሸነፈም።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
በሊጉ ሃዋሳ ከተማ በዘጠኝ ነጥብ አምስተኛ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአምስት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሃዋሳ ከተማ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ድሬዳዋ ከተማን በአራተኛ ሳምንት 2 ለ 0 በማሸነፍ ማስመዝገቡ ይታወቃል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቻል ከፋሲል ከነማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
መቻል እና ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ 10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የሚያሸንፈው ቡድን የሊጉ መሪ ይሆናል።