ማንቺስተር ሲቲን ከሊቨርፑል የሚያገናኘው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ መርሃግብር - ኢዜአ አማርኛ
ማንቺስተር ሲቲን ከሊቨርፑል የሚያገናኘው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ መርሃግብር
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2018(ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ሲቲ እና ሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካችን ቀልብ ስቧል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኢትሃድ ስታዲየም ይደረጋል።
ማንችስተር ሲቲ በሊጉ እስከ አሁን ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች 6 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ተሸንፎ በአንዱ ደግሞ አቻ በመውጣት 20 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎችን አስተናግዷል።
በ54 ዓመቱ ስፔናዊ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንችስተር ሲቲ በ19 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች 6 ጊዜ ድል ሲቀናው 4 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ 18 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።
በ47 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ አርን ስሎት የሚሰለጥነው ሊቨርፑል በ18 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 198 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሊቨርፑል 95 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ማንችስተር ሲቲ 50 ጊዜ ሲያሸንፍ 53 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 56 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 23 ጊዜ ሲያሸንፍ ማንችስተር ሲቲ 12 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 21 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።
ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ በሊጉ የሚያደርጉት ፉክክር ከእ.አ.አ 2010 አጋማሽ አንስቶ በየጊዜው እያደገና እየጋለ መጥቷል።
ማንችስተር ሲቲ ከባለፈው ዓመት ደካማ ብቃት በኋላ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አጀማመሩን በማሳመር ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሊቨርፑል ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም አራት ተከታታይ ሽንፈቶችን ማስተናገዱ ያልተጠበቀ ነበር።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ በዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር አስቶንቪላን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።
የዛሬው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ወሳኝ የሚባል ነው።
የ40 ዓመቱ ክሪስ ካቫናግ የሁለቱን ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ክሪስታል ፓላስ ከብራይተን፣ አስቶንቪላ ኮቦርንማውዝ፣ ብሬንትፎርድ ከኒውካስትል ዩናይትድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊድስ ዩናይትድ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።