ቀጥታ፡

72 የአጥቢ እንስሣት ዝርያዎች መገኛ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ

ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ውድምቢ የተሰኘው የዱር እንስሣ ኢትዮጵያ ውስጥ በብቸኝነት መገኛ እንደሆነም ይነገራል።

ማራኪ ዕይታና ድንቅ የተፈጥሮ አቀማመጥ የተቸረው ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ዙሪያ-ገባውን ሙርሲ፣ ቦዲ፣ ባጫ፣ ሙጉጂ፣ ኛንጋቶም፣ ሱርማ፣ ዲዚና ሚኒት ብሔረሰቦች አጅበውታል።

ፓርኩ በ1959 ዓ.ም. ሲመሠረት 4 ሺህ 68 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት እንደነበረው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ዋና ኃላፊ ኑሩ ይመር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ይህ አሃዝ በ2012/13 ዳግም በተደረገ የመከለል ሥራ ወደ 5 ሺህ 149 ስኩየር ኪሎ ሜትር ከፍ ማለቱንም ጠቅሰዋል።


 

72 የአጥቢ እንስሣት ዝርያዎች በፓርኩ ውስጥ እንደሚኖሩ የጥናት ውጤቶች ማመላከታቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ መካከልም አምሥቱ ትላልቅ የአፍሪካ አጥቢ እንስሣት መሆናቸውን ጠቁመው፤ እነሱም ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አውራሪስና ጎሽ እንደሆኑ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከ325 በላይ የአዕዋፍ፣ ከ24 በላይ የተሳቢና ተራማጅ፣ ከ13 በላይ የዓሣ ዝርያዎች እንደሚገኙ አስረድተዋል።

እንዲሁም ፓርኩ ከ600 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች መገኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ብሔራዊ ፓርኩን ከተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራት ለመጠበቅ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከመንግሥት መዋቅር ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም