ቀጥታ፡

በቁርጠኝነት ከተሰራ ከተማ እና ሀገርን መገንባት እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት - የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፦በቁርጠኝነት ከተሰራ ከተማ እና ሀገርን መገንባት እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።         

የአዲስ አበባ ከተማ ስኬት ለሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎች አርአያ እንደሚሆንም አመራር አባላቱ ገልጸዋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳር ልማት፣ የቤት ልማት እና አቅርቦት ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ መስጠፌ መሀመድ፤ በጉብኝቱ አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን እያካሄደች መሆኗን ተመልክተናል ብለዋል። 


 

በተለይም የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን የሚያጸኑ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን አይተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአመራሩ ቁርጠኝነት ሀገር መለወጥ የሚያስችል መልካም እድል መኖሩን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአዲስ አበባ  ያየናቸው የልማት ውጤቶች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ለማድረስ በትክክለኛው መስመር ላይ መሆናችንን አመላካች ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያን ትልሞች ከዳር በማድረስ ተጨማሪ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን ሲሉም ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መነቴ ሙንዲኖ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞችም ከፍተኛ ልምድ እንደሚሆን ተናግረዋል። 


 

ልማትን ቀጣይነት ባለው መልኩ እያረጋገጡ ለመሄድ ተግባራዊ እርምጃዎችን በላቀ ደረጃ የምንወስድበት ጊዜ ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም