ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት ዕይታ በዘርፎች ላይ የመጣውን እመርታዊ ለውጥ በተጨባጭ ማየት ችለናል - የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፦በመደመር መንግሥት ዕይታ በዘርፎች ላይ የመጣውን እመርታዊ ለውጥ በተጨባጭ ማየት መቻላቸውን የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም በሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአዳማ ከተማ መሰጠቱ ይታወቃል። 

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ላይ ያጠነጠኑ  ስልጠናዎችን ወስደዋል። 

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ትናንት በአዳማ ዛሬ ደግሞ በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት በግብርና እና ከተማ ልማት የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ፤ የብልጽግና ፓርቲ ብዝሃ ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ ድሎችን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

በግብርና ኢንዱስትሪ፣ በከተሞች ልማትና በቱሪዝም ዘርፎች የተደረጉ ሪፎርሞችና የተገኙ ውጤቶች የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መሰረት መጣላቸውንም አንስተዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ኢትዮጵያ ያላት ጸጋዎች ከራሷ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መሆኑን ያየንበት ነው ብለዋል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ ዘርፎች ላይ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችና ስለተገኙ ውጤቶች የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ሙስጠፌ እንዳሉት፤ በመደመር እይታ በፈጠራና በፍጥነት ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቀጣናው አልፋ ከዓለም አገራት ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንዳላትና ለዚህ ደግሞ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሰራ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሰተዳደር ጥላሁን እንደተናገሩት፤ በመደመር መንግሥት ዕይታ በዘርፎች ላይ የመጣውን እመርታዊ ለውጥ በተጨባጭ ማየት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም