ቀጥታ፡

የደን ሀብትን የማልማትና የመጠበቅ ባህልን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራን እንገኛለን-የደን ልማት ማህበር አባላት

ቦንጋ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የቆየውን የደን ሀብት የማልማትና የመጠበቅ ባህልን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰሩ እንደሚገኙ በካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ደን ልማት ማህበር አባላት ገለፁ።

የካፋ ዞን የበርካታ ተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም በዓለም በቅርስነት የተመዘገበው የበርካታ ብርቅዬ ብዝሃ-ህይወት መገኛው የካፋ ባዮስፌር አንዱ ነው። 

የካፋ ባዮስፌር በውስጡ ጥብቅ ደኖችንና ዘላቂ የልማት ሞዴልን የያዘ ሲሆን የአረቢካ ቡና፣ የበርካታ ሀገር በቀል ዛፎች፣ የመድኃኒት እፅዋት፣ የብርቅዬ እንስሳትና አእዋፋት ዝርያዎች መገኛ ነው።


 

በዚህ ባዮስፌር ውስጥም አሳታፊ የደን ልማት ማህበራት የሚገኙ ሲሆን ማህበራቱም በዞኑ የደን ሀብትን የማልማትና የመጠበቅ ባህልን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ።

በጊምቦ ወረዳ ሚቺቲ ቀበሌ ውስጥ ከሚገኙ የደን ማህበራት መካከል የበካ ደን ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ መብራቱ ገብረመስቀል  ከአያቶቻቸው የተረከቡትን ደን የመጠበቅ ባህልን ማስቀጠላቸውን ጠቅሰው ማህበራቸው 130 አባላትን ይዞ ከ600 ሄክታር በላይ መሬት የሸፈነውን ስፍራ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ከጥበቃው ጎን ለጎንም በክፍት ቦታዎች ላይ አዳዲስ ችግኞችን በመትከል የአካባቢው ስነ ምህዳር እንደተጠበቀ እንዲቆይ እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።

በአካባቢው ዘመናዊ የደን አጠባበቅ ስርዓት እንዲኖር ተደራጅቶ መንቀሳቀሱ ዘላቂ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የማህበሩ አባል አቶ ገረመው አሰፋ ናቸው።


 

ማህበሩ በስሩ ባሉት ስድስት ሳይቶች የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀርና የችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋም በየዓመቱ ተጨማሪ ችግኞችን በመትከል የደን መጠኑ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የካፋ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ወልደሚካኤል፣ የካፋ ማህበረሰብ  በደን አጠባበቅ ላይ የቆየ ልምድ አለው ብለዋል።  


 

ዘመናትን የተሻገረው የካፋ ማህበረሰብ የደን አጠባበቅ ባህል አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው ይህም በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በዚህም በዞኑ 66 ሺህ 500 ወንድና ሴት አባላት ያላቸው 265 ማህበራት ተደራጅተው ከ218 ሺህ 195 በላይ ሄክታር ደን በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

የካፋ ባዮስፌር የአረቢካ ቡና መገኛ ብቻም ሳይሆን ከአምስት ሺህ በላይ የቡና ዘረመሎች፣ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች እንዲሁም የተለያዩ አእዋፋት፤ ብርቅዬ የአንበሳ ዝርያና ሌሎች እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የካፋ ባዮስፌር 760 ሺህ ሄክታር መሬትን የሚሸፍን ሲሆን ከዚህም ውስጥ 52 በመቶው ጥብቅ ደን መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም