አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የሁሉም ተግባር መሆን አለበት -አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የሁሉም ተግባር መሆን አለበት -አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች
ነቀምቴ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፡ - አብሮነትና አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የሁሉም ተግባር መሆን አለበት ሲሉ አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች ተናገሩ።
በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ነገ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተውጣጡ አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ተካሄዷል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች፤ የክልሉ ሕዝብ አንድነት እና አብሮነቱን ይበለጥ በማጠናከር ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።
የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ወረቅና ተሬሳ እንዳመለከቱት፤ በየዓመቱ የሚከበረው ኢሬቻ የመከባበር ፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል ነው።
በመሆኑም ሕዝቡ በዓሉን ሲያከብር ለአንድነት ትስስር ቅድሚያ በመስጠት መሆን እንዳለበት ጠቅሰው ፤ ሁሉም ለዘላቂ ሰላም መስፈን በጋራ መቆም እንዳለበት አመልክተዋል።
አባ ገዳው፤ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ በመተሳሰብ እና በመተባባር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በጋራ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።
በተለይ እርስ በእርስ በመከባበር እና በመቻቻል የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ በሕብረት ማገዝ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሌላው አባ ገዳ ሀይሉ ለገሰ በበኩላቸው ፤ ሕዝቡ አብሮነቱን ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ አለበት ብለዋል።
ኢሬቻ የሰላም እና የመከባበር በዓል ነው ያሉት አባ ገዳው፤ በዓሉ ሲከበር አንድነትን እና ሰላምን አጉልቶ ማሳየት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሁሉም የሰላም ግንባታ እና ልማት ስራዎች ላይ ያለውን ድርሻ ማጠናከር እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ ሀደ ሲንቄ ትዕግስት ዲባባ ናቸው።
ሕዝቡ አንድነቱን በማጎልበት ሀገርን ለማሳደግ እና ለማልማት የተጀመረውን ጉዞ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።