ምሩቃን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች ለህገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች ለህገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ቡልቡላ ፤ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ):- ምሩቃን የፖሊስ አባላትና መኮንኖች ለህገ መንግሥቱ ታማኝ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በቡልቡላ መሰረታዊ ወታደራዊ የፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ ዙር ምልምል የፖሊስ ሰልጣኞችንና 2ኛ ዙር እጩ መኮንኖችን ዛሬ አስመርቋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
በተለይም የፖሊስ አባላት በታማኝነትና በቅንነት ህዝባቸውን በማገልገል ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የፖሊስ አባላት ማህበረሰቡን በስነ ምግባር በማገልገል የክልሉን ሰላምና ልማት ማጠናከር ላይ ያላቸውን ድርሻ እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል፡፡
የዛሬ ምሩቃን የፖሊስ አባላትና መኮንኖችም ለሰንደቅ ዓላማና ለህገ መንግሥት ታማኝ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የክልሉን ፖሊስ በሰው ኃይል በማደራጀት ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ምሩቃንም የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል የፖሊስ አገልግሎትን በመተግበር ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡
በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ለተልዕኮ ዝግጁ የሚያደርጉ ክህሎት በመጠቀም በታማኝነት ማህበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ድሪባ መኮንን እንደገለፁት የተጀመሩ የልማት እቅዶችን እውን ለማድረግ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ለዚህም የሁለቱን አጎራባች ክልሎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ የማህበረሰቡን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ ጉዞን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
"ኮሌጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ጎሳዬ ከበደ ናቸው፡፡
ኮሌጁ ክልላዊ ትስስርን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር የፖሊስ አካላትን ሲያሰለጥን መቆየቱን አስታውሰው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያግዙ ስልጠናዎች በብቃት እንደተሰጠም ተናግረዋል፡፡