ቀጥታ፡

ብልጽግና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ በሃሳብ ጥራት ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገበ  ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ በሃሳብ ጥራት ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም በሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየተሰጠ መሆኑ ይታወቃል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስልጠና በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ ስልጠናው በርካታ አዳዲስ የልማት ዕውቀትና እሳቤዎች የተሰጡበት ነው ብለዋል።

በስልጠናውም ላይ የኢትዮጵያን ቀጣይ አቅጣጫና አሁናዊ የልማት አቋም ታሳቢ በማድረግ አቅምና ክህሎትን የሚገነቡ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሃሳብ ጥራት ያለው፣ የገባውን ቃል በተግባር የሚፈጽም የሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ፓርቲው ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያስጠብቅና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የሀገራዊ አንድነት መገለጫ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ወደላቀ ከፍታ ለማሸጋገር በተከናወኑ ተግባራት በቱሪዝም፣ በገጠርና ከተማ፣ በኢንዱስትሪ የልማት መስኮች እመርታዊ ስኬት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዕድገት አለኝታ ተብለው በተለዩ የኢኮኖሚ መስኮች የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ስኬት መመዝገቡን አስረድተዋል። 

ስልጠናው የኢትዮጵያን ጸጋዎች ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ቁጭትና ተነሳሽነትን የፈጠረ ወሳኝ የአቅም ግንባታ መድረክ መሆኑን አንስተዋል። 

የአፋር ክልል የማዕድን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ ሁመድ፤ በስልጠናው የመደመር መንግሥትን የዘርፎች የመልማት ዕምቅ አቅም መገንዘባቸውን ገልጸዋል።


 

ስልጠናው የዘርፎችን የተሰናሰለና ተመጋጋቢ የልማት አቅም ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ያገኙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።  

የጋምቤላ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኳንግ ዑኳይ፤ የብልፅግና ፓርቲ ስልጠና ለቀጣይ ስራቸው ዕውቀትና ክህሎትን የቀሰሙበትና ዘመኑን የዋጀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቆይታቸውም የተሻለ አፈፃጸም ካስመዘገቡ የፌደራል ተቋማትና ክልሎች ልምድና ተሞክሮ መቅሰማቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም