የኢትዮጵያና ጃፓን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ጃፓን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ጃፓን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ገለጹ።
የጃፓን የባህል ቀን በዛሬው ዕለት የተለያዩ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና የተለያዩ ታዳሚዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሁለቱ አገራት መካከል በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለ።
የጃፓን መንግሥት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የትምህርት ዕድል መስጠቱን አመልክተው፤ በየጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የሥልጠና ፕሮግራሞች አማካኝነት በርካታ ሰልጣኞች ዕድሉን ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።
ጃፓንና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ይህም በአፍሪካ ከጃፓን የመጀመሪያዎቹ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች አንዱን እንደሚወክል ገልጸው፤ ግንኙነቱም በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህላዊና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
ጃፓን እንደ ትምህርት፣ ጤናና ግብርና ባሉ መስኮች የገንዘብና የቴክኒክ ትብብርን ማስፋፋቷን አንስተዋል።
የጃፓንና ኢትዮጵያን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርም ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል።
በባህልና እና ስፖርት ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ አህመድ መሀመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ጃፓን ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል እያበበ ላለው ሕያው የባህል ግንኙነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም መሰል በዓላት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው አመልክተዋል።