ጽንፈኛውን ቡድን ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም እንታገላለን - ኢዜአ አማርኛ
ጽንፈኛውን ቡድን ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም እንታገላለን
ወልዲያ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፡- በተለያዩ አጋጣሚዎች እገታና ዘረፋ እየፈፀመ ያለውን ጽንፈኛ ቡድን ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም እንታገላለን ሲሉ የአሽከርካሪዎች ማህበራት ተናገሩ።
"የባዳና የባንዳን ሴራ በማምከን አንፀባረቂ ድሎችን እናስመዘግባለን "በሚል መሪ ሀሳብ በወልዲያ ከተማ ከባጃጅ፣ ከታክሲና ሌሎች የተሽከርካሪ ማህበራት ጋር በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ፋሲካው መስፍን ፣አቶ ምህረቴ መኮንን እና ወጣት ጋሻው አለማየሁ በሰጡት አስተያየት፤ አሁን ላይ ሕዝቡ በሰላም መስራት፣ ወጥቶ መግባትና የልማት ስራዎችን ለማሳካት በከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዝቡ ፍላጎትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይህ ቢሆንም እየተሹለከለከ አገታ፣ ዘረፋና ግድያ እየፈፀመ ያለው ጽንፈኛ ቡድን ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በተለያዩ አጋጣሚዎች እገታና ዘረፋ እየፈፀመ ያለውን ጽንፈኛ ቡድን ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም እንታገላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት በመከላከያ ሰራዊት የ11ኛ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ፤ ጽንፈኛው ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር የህዝብን ሰላም ለማናጋትና የሀገርን ጥቅም ለማሳጣት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የህዝብ ጠላትና የልማት ጸር የሆነውን ጽንፈኛ ቡድን በመከታተል ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው እርምጃው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህ ጥረት ውስጥ የህዝቡን ትብብርና እገዛ አድንቀው፤ በወንጀል እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ አካላትን በማጋለጥና መረጃ በመስጠት ጭምር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።