ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት የሚከናወኑ የልማት ስራዎች አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በመደመር መንግሥት የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለአካታች ኢኮኖሚ ግንባታ እውን መሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የአባላቱን አቅም በሚገነቡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአዳማ ከተማ መሰጠቱ ይታወቃል።

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በሀገሪቷ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፎች ላይ ያጠነጠኑ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ዛሬ በአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት ስራዎች፣ የቤት ልማት እና አቅርቦት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስራ ሃላፊዎች እንደገለጹት ጉብኝቱ በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር ለመመልከት እድል ፈጥሮላቸዋል።


 

የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባኤ ኤልያስ ኡመታ በሰጡት አስተያየት አዲስ አበባ በአዲስ የልማት ስራ ተገልጣ የኢትዮጵያን እድገት በተግባር የምታሳይ ከተማ ሆናለች።

ውጤቱ በመደመር መንግሥት በጋራ በመስራት የተገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ለብዝሃ የልማት አቅጣጫ የሰጠው ትኩረት ውጤት እያመጣ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጣቸውን በተጨባጭ መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ያደረገው የለውጥ ስራ በእጅጉ የሚበረታታና ለክልሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኝ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ ስልጠናው ዋና ዋና የልማት መስኮችን በመለየት ወደ ተግባር መቀየር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።


 

በተለይም ክልሎች ያላቸውን እምቅ ሃብት ለኢኮኖሚ ምንጭነት መጠቀም የሚችሉበትን አቅጣጫ ያመላከተ ሰለመሆኑም አንስተዋል።

በተለይም በሁሉም አካባቢዎች ለቱሪዝም ልማት የሚጠቅሙ ሀብቶች እንዳሉ መገንዘብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን መሸጋገራችንን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚታየው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለሌሎች መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት የግል አልሚዎችንና ማህበረሰቡን በማሳተፍ የሚያከናውነው የልማት ስራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።


 

የጋምቤላ ክልል የህብረት ስራ ማህበራት እና ማደራጃ ኤጀንሲ ሃላፊ ፓራሎክ ዋዋ ስልጠናው ለቀጣይ ስራቸው ትልቅ ግብዓት ያገኙበት መሆኑን  ገልጸዋል።

በተለይም ክልሎች ያላቸውን ሀብት ወደ ጥቅም የሚቀይሩበትን ዕድልና አማራጭ በማስፋት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አስችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም