የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማሳደጊያ ተግባር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው
ሮቤ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦የጡት ካንሰር መነሻ ምክንያት እና መከላከያ መንገዶች የግንዛቤ ማሳደጊያ ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ የእናቶችን ህይወት ለመታደግ ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከሩን የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ገለጸ።
ሆስፒታሉ የጡት ካንሰር በሽታ መነሻ ምክንያት እና መከላከያ መንገዶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ የውይይት መድረክ ዛሬ በሮቤ ከተማ አካሂዷል።
በተለይም ለጡት ካንሰር በሚያጋልጡ ምክንያቶች ላይ ግንዛቤን በማሳደግ የእናቶችን ህይወት ለመታደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከሩም ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐመድአማን ማማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ የካንሰር ህክምናን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።
ጥቅምት ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ መፍጠሪያ ወር መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ ስለበሽታው ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ በተለያዩ አካባቢዎች ጊዜያዊ ጣቢያዎችን በማቋቋም ለህብረተሰቡ ከሚሰጠው የግንዛቤ ፈጠራ በተጨማሪ ነፃ የምርመራና የምክር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በጡት ካንሰር ልየታና ቅድመ ምርመራ ላይ እያደረጉ የሚገኙት ሥራና የግንዛቤ መፍጠርያ ተግባራት የጥረቱ አካል መሆኑን አንስተዋል።
በሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አዲስ ጉልላት፣ አብዛኛው የካንሰር ታማሚ የበሽታው ደረጃ ከፍ ካለና ከተሰራጨ በኋላ ለህክምና ስለሚመጡ ህክምናውን ከባድ እያደረገው መሆኑን አመልክተዋል።
የጡት ካንሰር በሽታ ቀድሞ ከተደረሰበት በሕክምና ሊድን እንደሚችል ያመለከቱት ዶክተር አዲስ፣ ለዚህም ህብረተሰቡ በቅድመ ልየታ ራሱን እንዲያውቅ ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ መስራት ይገባል ብለዋል።
ህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤውን በመቀየር በተለይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግና ራሱን ከሱስ በማራቅ የካንሰር በሽታን መከላከል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የጡት ካንሰር በሽታ ሕክምናን በአግባቡ በመከታተል እንደሚድን የተናገሩት ደግሞ ከበሽታው በሕክምና እንደዳኑ የገለጹትና በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሮቤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር ከተማ ናቸው።
በሽታው ኖሮባቸው ተደብቀው የሚኖሩ እናቶች እንዳሉ የተናገሩት ወይዘሮ አስቴር፣ በጤና ተቋም ታክሞ መዳን እንደሚቻል ራሳቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
ሴቶች በተለይም እናቶች "የካንስር በሽታ ዘመናዊ ህክምና አይወድም" በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን መታዘባቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አለም ጸጋ ናቸው።
ስለበሽታው ባገኙት ግንዛቤ የካንሰር ቅድመ ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን ለማወቅና ሌሎችንም ለማስተማር መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ለጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት መከላከልና የህክምና ክትትል በማድረግ መዳን እንደሚቻል ከውይይቱ ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች እንደሚያካፍሉ የገለጹት ደግሞ ሀደ ሲንቄ አባይ በቀለ ናቸው።
በሆስፒታሉ ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር የግንዛቤ መፍጠሪያ ወር በነፃ ምርመራና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ በሌሎች መርሀ ግብሮች ተካሂዷል።