የደመወዝ ማሻሻያው የሥራ ተነሳሽነታችንን ይበልጥ አጠናክሮልናል - የመንግስት ሠራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የደመወዝ ማሻሻያው የሥራ ተነሳሽነታችንን ይበልጥ አጠናክሮልናል - የመንግስት ሠራተኞች
አምቦ ፤ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፡-መንግስት ያደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የሥራ ተነሳሽነትን ይበልጥ በማጠናከር የተገልጋይ እርካታን ለማረጋገጥ እንዳበረታታቸው በአምቦ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት የመንግስት ሠራተኞች፤ የደመወዝ ማሻሻያው የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ በቀጣይ ሕዝቡን በላቀ ቁርጠኝነትና ብቃት ለማገልገል ብርታት እንደሆናቸው ገልጸዋል።
የከተማው አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ፤ በተደረገላቸው የደመወዝ ማሻሻያ ደስተኛ እንደሆኑ በመግለፅ ይህም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንደሚያግዝ ተግረዋል፡፡ የሥራ ተነሳሽነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ያበረታታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ አቶ ታደሰ ለገሰ በበኩላቸው፤ መንግስት ያደረገው የደመወዝ ማሻሻያ ተገቢ እና ወቅታዊ ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።
ይህም ሕብረተሰቡን በበለጠ ፍጥነትና ጥራት በማስተናገድ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር እንዳበረታታቸው ገልጸዋል።
የደመወዝ ማሻሻያው የመንግስት ሠራተኞች የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ የአምቦ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ ወይዘሮ ትእግስት ፈይሳ ናቸው።
ማሻሻያው ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚቀንስ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ህገ ወጦች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
የአምበ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አራርሳ ከበደ፤ የመንግስት ሠራተኛ የደመወዝ ማሻሻያው በከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
በዚህም ሠራተኛው ደስተኛ መሆኑን አንስተው፤ ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እርካታን ለማረጋገጥ መትጋት እንዳለበት አስገንዘበዋል።