ቀጥታ፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን በተመረጡ ቀበሌዎች የገጠር ኮሪደር ልማት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጎንደር ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦በማእከላዊ ጎንደር ዞን በያዝነው ዓመት በተመረጡ ቀበሌዎች በገጠር ኮሪደር ልማት የሞዴል የአርሶ አደሮች መንደርን ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ  እንደገለጹት የገጠር ኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ በማሸጋገር በገጠሩና በከተማ መካከል የተሳሰረ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመፍጠር የሚያስችል ነው።

የገጠር ኮሪደር ልማቱ በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎች በተመረጡ 15 ሞዴል የገጠር ቀበሌዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

የገጠር ኮሪደር ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወጥ የሆኑ የሞዴል አርሶ አደሮች መንደሮችን ለመገንባት የሚያስችል ንድፍ እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማቱ የሞዴል አርሶ አደሮች መኖሪያን ጨምሮ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የመንገድ፣ የመጠጥ ውሃና አማራጭ የኢነርጂ  መሰረተ ልማቶችን ባካተተ መልኩ እንደሚገነባ አስረድተዋል።

ለገጠር ኮሪደር ልማቱ የተመረጡ ቀበሌዎች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡና በተጨባጭ የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየር ሞዴልነታቸውን ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማቱ በገጠር የሚኖረውን ሰፊ ቁጥር ያለውን አርሶ አደር የእውቀት፣ የዘመናዊነትና የቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ማድረግ የሚያስችል አዲስ ሃሳብና ራእይ የያዘ ነው ያሉት ደግሞ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ክንዱ ዘውዱ ናቸው፡፡


 

የገጠር ኮሪደር ልማቱ የገጠሩን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ጠቁመው ፍትሃዊና የተመጣጠነ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያሰፍን በመሆኑ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስረሳው ደሴ በበኩላቸው በዚህ ዓመት በወረዳው የኮሪደር ልማቱን ለማስጀመር አንድ ሞዴል የገጠር ቀበሌ መመረጡን ተናግረዋል፡፡


 

ለገጠር ኮሪደር ልማቱ የሚያስፈልገውን የሎጂስቲክስ፣ የባለሙያዎች፣ የበጀት ድጋፍ የማስተባበርና የማደራጀት ስራዎች መጠናቀቁን ጠቁመው የሞዴል አርሶ አደሮች መንደር ቅየሳ አሁን ላይ መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማቱ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ሀገሪቱ ወደ ብዝሃ ኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ የጀመረችውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ እድገት የሚያፋጥን መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም