የዓመታት ጥያቄ ሆኖ የቆየው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራችን መፍትሄ አግኝቷል - የዋቻ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዓመታት ጥያቄ ሆኖ የቆየው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራችን መፍትሄ አግኝቷል - የዋቻ ከተማ ነዋሪዎች
ቦንጋ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ ዞን የዋቻ ከተማ የዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍትሄ ማግኘቱን ነዋሪዎች ገለጹ።
መንግስት የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችለውን የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
ከነዚህም ተግባራት መካከል በተለይ በገጠሩ አካባቢ የህክምና፣ የትምህርትና ሌሎች ተቋማትን በመገንባት የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የማሳደግ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ማህበራዊ ችግሮችን ከመፍታት አንፃርም በከተማና በገጠር ለሚገኙ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ለዓመታት ለቆዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።
በዚህም ተጠቃሚ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የዋቻ ከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ስራ መጀመር ለረጅም ዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ለቆየው ችግር መፍትሄን ይዞ እንደመጣም ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑን አቶ ጌታቸው አስፋው፤ ከዚህ ቀደም በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ይቸገሩ እንደነበረ ጠቁመው በክልሉ መንግስት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ፕሮጀክትም ችግሩን ሙሉ በሙሉ አስወግዶታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከመመረቁ በፊት ምንም አይነት የቧንቧ ውሃ በከተማው እንዳልነበረና የጉድጓድና የምንጭ ውሃ ለመጠጥ ይጠቀሙ እንደነበረ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ መላኩ ካፍትይመር ናቸው።
ችግራቸው እንዲፈታላቸው ለበርካታ ጊዜያት ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ አጥተው በጫና ውስጥ እንደቆዩና አሁን በለውጡ መንግስት የውሃ ፕሮጀክቱ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ትልቅ እፎይታ እንዳገኙ ተናግረዋል።
ወይዘሮ የሺ መልካ በበኩላቸው አካባቢው የጉድጓድ ውሃን በቀላሉ ቆፍሮ ለማውጣት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ ተመርቆ ስራ በመጀመሩ ለችግራቸው መፍትሄን እንዳመጣ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዓመታት የቆየውን የህብረተሰቡን ጥያቄ በመመለስ ትልቅ እፎይታን የፈጠረ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሁነኛው ታደሰ ናቸው።
ይህም የለውጡ መንግስት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው ብለዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆን ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን ገልፀው በቀጣይም አገልግሎቱ ያልተዳረሰባቸው ሰፈሮችን በመለየት የማስፋፊያ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከተመረቀበት ጊዜ አንስቶ ያለ ምንም መቆራረጥ አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ረጅም ጊዜ እንዲያገለግልም አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወሳል።