ቀጥታ፡

 በዞኑ በክረምት ወራት የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአብሮነት እሴቶችንና የሰላም ግንባታን አጠናክሯል

አዶላ ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦ በጉጂ ዞን በክረምት ወራት የተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአብሮነት እሴቶችንና የሰላም ግንባታን ማጠናከሩን የዞኑ ነዋሪዎች ገለፁ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች እንደገለፁት አገልግሎቱ በዞኑ የህዝብ ለህዝብ የመረዳዳት፤ የሰላም ግንባታ፤ የልማትና የአብሮነት ባህላዊ እሴቶች እየተጠናከሩ እንዲመጡ እያደረገ ነው፡፡

በዞኑ የአዶላ ከተማ ነዋሪው አቶ ጌታቸው ጎልጃ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች እያቃለለና የመረዳዳት ባህልን እያሳደገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይም በበጎ ፈቃደኞች እየተተገበረ ያለውን መልካም ስራ በማስቀጠል ረገድ በአቅማችንን በመሳተፍ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ነባሩን የህዝብ ለህዝብ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት እያጎለበተ እንደመጣ የጠቆሙት ደግሞ ሌላኛው  የከተማው ነዋሪ አቶ ገመቹ ቱሉ ናቸው፡፡

በጎ ፈቃድ ማህበራዊ ችግሮችን ከማቃለል ሌላ በሰላም ግንባታ፣ በልማት በሙያና በእውቀት ሽግግር የስራ ልምድና ባህልን እያሳደገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአዶላ ወረዳ የኦዳ ዶላ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዙፋን ተፈራ በበኩላቸው በእርጅና ምክንያት በፈረሰ ቤት ውስጥ ከ7 ልጆቻቸው ጋር ለዓመታት በክረምት ዝናብና በበጋ ጸሀይ እየተፈራረቀባቸው አስከፊ ህይወት እንዳሳለፉ ተናግረዋል፡፡

''ዘንድሮ በበጎ ፈቃደኞች በተሰራልኝ ቤት ትልቁ ሸክሜ ተቃሎልኝ እየኖርኩ እገኛለሁ'' በማለት ለበጎ ፈቃደኞቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 

በጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ክትትል ኃላፊ አቶ ሙለታ መኩሪያ እንደተናገሩት፤ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋነኝነት በትምህርት፣ በጤና፣ በሰላም ግንባታ፣ በግብርናና በአረንጓዴ አሻራ ልማት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች 145 ኪሎ ሜትር የመንገድ፣ 206 የድልድይ፣ 89 የመማሪያ ክፍሎች፣ ለ6 ሺህ  አረጋውያን የአዲስ ቤት ግንባታና እድሳት በበጎ ፈቃደኞች መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ወባና መሰል በሽታዎችን የመከላከል እንዲሁም የከተሞች ጽዳትና ውበት ስራ መከናወኑን ገልጸው 450 ዩኒት ደም መለገሱንም አክለዋል።

በተጨማሪም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች የመማሪያ ወንበርና ጠረጴዛ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል። 

በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የወተት ላሞች፣ የእንቁላል ዶሮዎች፣ በግና ፍየሎች መከፋፈላቸውን አስታውሰዋል፡፡

በቆላማ ወረዳዎች የድርቅ ተጋላጭነትን ለመከላከል በማለም ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዞኑ ባለፉት አራት ወራት በተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት የመንግስትና የህዝብ ሃብትን ማዳን እንደተቻለም አመልክተዋል፡፡ 

በዞኑ በክረምት ወራት የተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወቅትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም