በደም እጦት የሰው ህይወት እንዳያልፍ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፎ ማደግ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በደም እጦት የሰው ህይወት እንዳያልፍ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፎ ማደግ አለበት
አዳማ ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በደም እጦት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት የክልሉ ጤና ቢሮ አመለከተ።
ቢሮው የዘንድሮ የደም ልገሳ ዕቅዱን ለማሳካት ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በትብብር ለመስራት የንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል ።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ቦኮና ጉታ በወቅቱ እንደገለፁት በደም እጦት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት 130 ሺህ ዩኒቲ ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ በሩብ ዓመቱ ከ38 ሺህ ዩኒቲ በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በበጀት አመቱ ለመሰብስብ የታቀደውን የደም መጠን ለማሳካት ከትምህርት ቤቶች፣ ከኃይማኖት አባቶች ፣ከወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ጋር የንቅናቄ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የዛሬው ንቅናቄም ከ150 ትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ ለመስራት የምክክር መድረክ መካሄዱን ተናግረዋል ።
ደም መለገስ በህመምና በድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም በወሊድ ወቅት ደግሞ እናቶች በደም እጦት ህይወታቸው እንዳያልፍ የሚደረግ በጎ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በክልሉ በደም እጦት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተሳትፎ ማደግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በምክትል የቢሮ ሃላፊ ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ኤፍሬም ተሰማ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች ትውልድን በዕውቀትና በአመለካከት ከመቅረፅ ባለፈ ህይወት በመታደግ ረገድ በንቃት እየተሳተፉ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ በዜግነት አገልግሎት ከሚሰጡ ተግባራት መካከል የተማሪዎች የደም ልገሳ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በትምህርት ቤቶች ደም የመለገስ በጎ ተግባርን ለማሳካት የድርሻቸውን በመወጣት ምትክ የሌላትን ህይወት ለመታደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በባሌ ሮቤ ከተማ የጄኔራል ዋቆ ጉቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ደሳለኝ ዱጋ እንደተናገሩት ደም መለገስ የበጎ ተግባር ሁሉ ማሳያ ነው።
ደም ሲለግሱ የሰው ልጆችን ህይወት መታደግ በመሆኑ ተማሪዎች ደም በመለገስ እንዲረባረቡ የንቅናቄ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ።
በትምህርት ቤቱ አምና 940 ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልፀው በተያዘው በጀት ዓመትም ከ1ሺ በላይ ዩኒቲ ደም ለመሰብሰብ አቅደናል ብለዋል።