ቀጥታ፡

በአማራ ክልል  የምግብ ሉዓላዊነትን  ለማረጋገጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኮምቦልቻ ፤  ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የምግብ ሉዓላዊነትን  ለማረጋገጥ  የበጋ መስኖ  ስንዴ ልማት ይበልጥ ተጠናክሮ  መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለመስኖ ባለሙያዎች ስልጠናና የመስኖ ልማት ንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ  ቃልኪዳን ሽፈራው እንዳሉት፤ በክልሉ በመስኖ የሚለማ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መኖሩን ጥናታዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአጠቃላይ በክልሉ ከ383 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ በማልማት ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም 260 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ በማልማት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ለማምረት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በበጋ መስኖ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርትን በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋትም በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ  አሳልፍ አህመድ፤ በዞኑ 21 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በስንዴ በማልማት ከ860 ሺህ ኩንታል በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።


 

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ባለፉት ዓመታት የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም  ወዳልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ የመስኖ ስንዴ ልማትን በማስፋት  የምግብ ሉዓላዊነትን   ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል   የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አስካል ይፍሩ ናቸው።


 

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወቅት  27 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ቦጋለ መንግሥቱ፤ በዞኑ ከ6 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና  የከተማ አስተዳደር  አመራሮች፣ የመስኖ ልማት ባለሙያዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም