በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ እየተጋን ነው -- የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ እየተጋን ነው -- የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች
ጊምቢ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፦በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየተጉ መሆኑን በምእራብ ወለጋ ዞን የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ከተሰማሩ የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ በልዩ ደጋፋ እንዳሉት ቀደም ሲል በአነስተኛ ንግድ ስራ ተሰማርተው ህይወታቸውን ይመሩ ነበር።
በሚያገኙት ገቢም የቤተሰባቸውን ፍጆታ ለማሟላት ይቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መሳተፍ ከጀመሩ ወዲህ ህይወታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ግንዛቤ እና ስልጠና በአሳማ እርባታና በሌሎች የከተማ ግብርና ስራዎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
የአሳማ እርባታው ውጤት በአጭር ግዜ እየታየ በመምጣቱ ልምዳቸውን ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያካፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአሳማ እርባታ ጎን ለጎን የሚያካሄዱት የከተማ ግብርናም ገቢያቸውን ከማሳደግ አልፈው ለቤተሰባቸው የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ አስፋው አያና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተሰማርተው የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ስራውን በማስፋፋት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል ለመፍጠር ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች እርባታ ላይ የተሰማሩት አቶ ሳቀታ ፊሪሳ በበኩላቸው ከ3 ላሞች በየቀኑ እስከ 20 ሊትር ወተት በማግኘት ገቢያቸውን እያሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳት ልማትና ዝርያ ማሻሻል ቡድን መሪ አቶ ገመቺስ ታደሰ፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የዞኑ አርሶ አደሮች በጥምር ግብርና የሚያደርጉት ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በተለይም የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች ለዞኑ አርሶ አደሮች እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰው የዶሮ እርባታ ስራም እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዞኑ በዶሮ እርባታ ለተሰማሩ ነዋሪዎች ከ3 ሚሊዮን በላይ የዶሮ ጫጩቶች መከፋፈላቸውን ገልጸው 12 ሺህ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጊደሮችም በሰው ሰራሽ ዘዴ መዳቀላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩም ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ እና ገቢውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤትም ሙያዊ ድጋፍ እና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ሚናውን እያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰዋል።