በምዕራብ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ሰብል ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ሰብል ይጠበቃል
ገንዳ ወሃ፤ ጥቅምት 29/2018(ኢዜአ)፡ - በምዕራብ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ በበጋ መስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚደግፍ የመስክ ምልከታ ተካሄዷል።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ጤናው ፋንታሁን፣ ዞኑ በመስኖ መልማት የሚችል ሰፊ መሬትና የውኃ አቅም መኖሩን አመላክተዋል።
ይሁን እንጅ በመስኖ ልማት የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና የሚሸፈነው መሬት ዞኑ ባለው እምቅ ሀብት ልክ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ አመት ከ3 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት፣ ፍራፍሬና አዝዕርት የሚለማ መሆኑን ገልፀው በዚህም ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በዞኑ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ፓፓያ፣ ሎሚ፣ ሙዝ እና ሌሎችም የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶች በብዛት የሚመረቱ ሲሆን በቆሎና የበጋ መስኖ ስንዴም የሚለማ መሆኑን ገልፀዋል።
በበጋ መስኖ ልማት ከሚሳተፉ አርሶአደሮች መካከል አርሶአደር ሙሀመድ ገደፋው እንዳሉት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ጎመን ለማልማት አቅደዋል ።
እስካሁን ሩብ ሄክታር የሚሆነውን በዘር መሸፈናቸውን ገልፀው በቀጣይ እቅዳቸውን ለማሳካት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።
ሌላኛው አርሶአደር አደም ሁሴን በበኩላቸው በአንድ ሄክታር ከግማሽ በሆነ መሬት ላይ ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ አዝዕርት ሰብሎች የሚያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ቋሚ የፍራፍሬ ችግኞችን ከግብርና በማግኘቴ ፓፓያና ማንጎ እያለማሁ ነው ያሉት አርሶአደሩ ፓፓያው ደስ በሚያሰኝ መልኩ ማፍራት መጀመሩን ተናግረዋል።