የምሥራቅ ዕዝ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ተልዕኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት መወጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል-ሜጀር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ ዕዝ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ተልዕኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት መወጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል-ሜጀር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ
ጅግጅጋ፤ጥቅምት 29/2018 (ኢዜአ)፡-የምሥራቅ ዕዝ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና ተልዕኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት መወጣቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠሉን የዕዙ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ ገለጹ።
ዕዙ በማሰልጠኛ ማዕከሉ የአቅም ግንባታ ማጠናከርያ ስልጠና የሰጣቸውን ወታደሮች አስመርቋል።
በምረቃው ሥነ- ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀnራል ፍቃዱ ፀጋዬ እንደገለጹት፤ ዕዙ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ደሕንነት በላቀ ብቃትና ጀግንነት እያስጠበቀ ይገኛል።
በተለይ ዕዙ በተለያዩ ጊዜ የተሰጠውን ተልዕኮና ግዳጅ በላቀ ብቃት ስኬታማ አፈፃፀም እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዝቦችን ሰላምና ደሕንነት የሚነሱ ጽንፈኞችንና ተላላኪዎችን በመደምሰስ አኩሪ ገድል መፈፀሙንም አንስተዋል።
የምሥራቅ ዕዝ በየተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና እና አካባቢ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት፣ ቁርጠኝነትና ጀግንነት መወጣቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠሉን ሜጀር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ አረጋግጠዋል።
ስልጠናውም የሠራዊቱ አባላት በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ለሚፈጠር የፀጥታ ስጋት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችልና የተሟላ የዝግጁነት ቁመና የገነባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የሠራዊቱ አባላትም በማዕከሉ ያገኙትን ክሕሎት በመጠቀም ሕገ መንግስታዊና ተቋማዊ ተልዕኮን በጀግንነት ታጥቀውና ሕዝባዊ ባሕሪ ተላብሰው መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የምሥራቅ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ኮለኔል አሊ ሰዒድ በበኩላቸው፤ ተመራቁ የሰራዊቱ አባላት ከዕዙ የተለያዩ ኮሮች የተውጣጡ መሆናቸወን ተናግረዋል።
የሠራዊቱ አባላት በማዕከሉ ቆይታቸው ዘመናዊ ወታደራዊ ዕውቀትና ጥበብ የቀሰሙ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በስልጠና ቆይታቸው ያገኙት እውቀትም የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት እንዲወጡ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖች፣የሶማሌና ሐረሪ ክልል የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ሌሎች አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።